አቶ ዮሃንስ ቧያለው ተቋሙን እንዲመሩ ሲሾሙ በስሙ ምክንያት ኃላፊ መሆን እንደማይፈለጉ በመግለጽ ሹመቱን ሳይቀበሉት ቀርተው ነበር
አቶ ዮሃንስ ቧያለው ተቋሙን እንዲመሩ ሲሾሙ በስሙ ምክንያት ኃላፊ መሆን እንደማይፈለጉ በመግለጽ ሹመቱን ሳይቀበሉት ቀርተው ነበር
የመንግስት ተቋም ሆኖ ወደ ሥራ የገባው መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ስያሜው ሊቀየር መሆኑን የአካዳሚው ሰራተኞች አስታወቁ፡፡
የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ እንደገለጸው የአካዳሚውን ተልዕኮ የሚመጥን ስያሜ ለመስጠትም ስራ ሲሰራ እንደነበር አስታውቋል፡፡
እስካሁን መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ሲባል የነበረው የመንግስት ተቋም የኢትዮጵያ አመራር አካዳሚ እንዲባል ሀሳብ መቅረቡ አል ዐይን ከተቋሙ አረጋግጧል፡፡ ይሁንና ሀሳቡ ገና በሕግ አጽዳቂው አካል እንዳልጸደቀ ተገልጿል፡፡
ተቋሙ የሪፎርሙ ቴክኒካል ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን አረጋ የተቋማት ስያሜ የራሳቸው የሆኑ ሳይንሳዊ መስፈርቶችን በመከተል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው ከአካዳሚው ጋር ተመሳሳይ ተልዕኮ ያላቸውን 19 ተቋማትን ከተለያዩ ሃገራት በመለየትና በመውሰድ ስያሜያቸውን የማጥናት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሰረት ከ8 እስከ 10 የሚደርሱ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን በማስቀመጥ አካዳሚው ሊኖረው የሚገባው ስያሜ ላይ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ለስያሜው በቀረቡት አማራጮች ላይ ውይይት እንደተደረገበት ሀገርን የሚወክል ስያሜ መሆን አለበት የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት ማግኘቱን አቶ ጥላሁን አስታውቀዋል፡፡
የተቋሙ ስያሜ ሁሉን አቀፍና አብዛኛውን የሚያስማማ እንዲሆን መታመኑን የገለጹት አቶ ጥላሁን ሀሳቡም ለጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ ቤት እንደቀረበ አስታውቀዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የቦርድ ሰብሳቢነት ናቸው፡፡አቶ ዮሐንስ ቧያለው የካቲት 2012 ዓ.ም የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸው የሚታወስ ሲሆን “ አሁን ተቋሙ ባለው የሕዝብ አመለካከት በተቋሙ መሥራት የምችልበት ሁኔታ ስለሌለ የቀረበውን ሹመት ለመቀበል ያስቸግረኛል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት አቶ አወሉ አብዲ አካዳሚውን እንዲመሩ መሾማቸው ይታወሳል፡፡