ንቅናቄው 10 አባላቱን ከአባልነት እንዲታገዱ መወሰኑንም አስታውቋል
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የንቅናቄውን ህግ ጥሰዋል በሚል 10 አባላቱን ከአባልነት አገደ፡፡
አብን ባወጣው መግለጫ ከድርጅት ህገ-ደንብ እና አሰራር ውጭ በመሆን አፍራሽ ድርጊቶችንና የዲሲፕሊን ጥሰቶችን በፈፀሙ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ላይ የእርምት እርምጃ መወሰኑን ገልጿል፡፡
የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም አደረኩት ባለው አስቸኳይ ስብሰባ በፓርቲው መዋቅር የተለያዩ የሃላፊነት እርከኖች ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ የዲሲፕሊን እና ድርጅታዊ መርህ ጥሰቶችን በፈጸሙ አባላቱ ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡
በዚህም መሰረት የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ የንቅናቄው ስራ አስፈጻሚ ሆነው ሳለ አፍራሽ ተልዕኮን ሲያረራምዱ ተገኝተዋል በሚል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ተብሏል፡፡
አቶ ክርስቲያን የተጣለባቸውን ከፍተኛ ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው በተለያዩ አፍራሽ ድርጊቶች ላይ የተሳተፉ ሲሆን ከዚህ ቀደም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሁለት ጊዜ የቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው እንደነበርም ተገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ አቶ ክርስቲያን በንቅናቄው ሥራ አስፈፃሚነታቸውም ሆነ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው በጋራ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ተገዥ ባለመሆን እና ንቅናቄውን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ አንጃዎች ጋር ሕብረት ፈጥረው ንቅናቄው የሃሳብና የተግባር አንድነት እንዳይኖረው በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ስለተገኙ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ተወስኗል ብሏል ፓርቲው ባወጣው መግለጫ፡፡
“መንግስት ግድያ ከሚፈጽሙ ኃይሎች ራሱን መነጠሉን ማረጋገጥ አለበት”-አብን
አብን ከዚህ በተጨማሪም በፓርቲው መዋቅር ውስጥ በተለያየ የሃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ የንቅናቄው መካከለኛ አመራሮችና አባላት የሆኑት አቶ አንተነህ ስለሺ መርዕድ፣ አቶ እሱባለው ሙላት ዘለቀ፣ አቶ ንጉሥ ይልቃል ያለው፣ አቶ ዓለሙ ወልዴ አከለ፣ ዶ/ር ጌታሁን ሣህሌ ወልዴ /የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል/፣አቶ የማነ ብርሃን ሙጬ፣ አቶ ጓዴ ካሴ ወልዴ፣ አቶ ስንታየሁ ተስፋው ስዩም፣ አቶ እስክንድር ለማ በቀለ እና አቶ ጌታነህ ወርቁ ይርዳው ከአባልነት እንዲታገዱ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
አባላቱ በድርጅት አመራርነት የተጣለባቸውን ሃላፊነት ወደጎን በመተው በፓርቲው ስራ አስፈጻሚም ሆነ ማዕከላዊ ኮሚቴ ወይም ጠቅላላ ጉባኤ የጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅትን በሚመለከት የተሰጣቸው ውክልና ሳይኖር፣ የጠቅላላ ጉባኤ ተወካይ ነን በማለት ህገወጥ ቅስቀሳና አድማ መምራትና በንቅናቄው ውስጥ አንጃ መፍጠር፤ የጉባኤ አባላትን በተለያዩ አሉባልታዎች በማደናገር እና የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ፊርማ ማሰባሰብ፣ ህገወጥ የጠቅላላ ጉባኤ ውክልና ይገባኛል መጠየቅና ድርጅታዊ ሥልጣን በእጅ አዙር ለመንጠቅ መሞከር፤ ከንቅናቄው እውቅና ውጭ የሆኑ የቴሌግራም ቡድኖችን በመክፈት አፍራሽ ቅስቀሳዎችን ማድረግ፤ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት ምንም አይነት ስልጣን ሳይኖራቸው፣ ጉባኤ ጠርተን ሪፎርም እናካሂዳለን በማለት ከድርጅቱ እውቅና ውጭ ገንዘብ አሰባስበዋል የሚሉ ጥፋቶችን ጭምር ፈጽመዋል ተብሏል፡፡
እንዲሁም አባላቱ የድርጅቱን ደንብ ተላልፎና ከሚመለከተው ክፍል ፈቃድ ሳይኖር በየሚዲያው መግለጫ መስጠት፣ ድርጅታዊ ምሥጢር ማባከን በንቅናቄው ላይ መሰረተ ቢስ ክሶች በመሰንዘር እና በከፍተኛ አመራሩ ላይ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ መክፈታቸውንም ንቅናቄው ገልጿል፡፡
ፓርቲው አቶ ሀብታሙ በላይነህ መኮንን እና አቶ በቀለ ምንባለ አምሳሉ ለተባሉ አባሎቹ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መስጠቱንም አክሏል፡፡
እነዚህ ሁለት የፓርቲው አባላት የንቅናቄው ቋሚ ኮሚቴዎች አባላትና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው እያለ በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አብረው ውሳኔ ያሳለፉበትን አጀንዳ በእጅ አዙር ለመቀልበስ አባላትን በማሳደም ፤ ለንቅናቄው የስብሰባና ሥነስርዓታዊ ህጎች፣ እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት ባለመገዛትና የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎችን ረግጦ በመውጣት ተደጋጋሚ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን ፓርቲው በመግለጫው አስቀምጧል፡፡