ፕሬዝዳንቷ ጋር የሚቀርበው የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ አባላት በፓርላማው ፀደቀ
ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ስልጣን የተሰጠው ጉባዔው ከ 11 አባላት አሉት
አጣሪ ጉባኤ አባላት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ነው የሚሾሙት
የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ 11 አባላት ያሉት ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ ስድስቱ የህግ ባለሙያዎች እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ደንግጓል።
ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ስልጣን የተሰጠው ጉባዔው ከ 11 አባላት አሉት። ስድስቱ አባላትም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የሚሾሙ ሲሆን በሙያ ብቃታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው መሆን እንዳለባቸው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 82 ተቀምጧል።
ዛሬ ታሕሳስ ሰባት ቀን 2014 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ስድስቱ የሕግ ባለሙያዎች በፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ አማካኝነት እንዲሾሙ ምክር ቤቱ ወስኗል።
ዛሬ ለጉባዔው አባልነት በዕጩነት ከተመረጡት ስድስት የሕግ ባለሙያዎች ውስጥ አምስቱ ለዚህ ቦታ አዳዲሶች ናቸው።
የቀድሞው ጉባዔ የሥራ ዘመኑን ሀምሌ 2013 ዓ.ም ያጠናቀቀ ሲሆን የጉባዔው አባል የነበሩትና ከ 2007 ዓ.ም ጀምሮ አባል የነበሩት ወ/ሮ ደስታ ገብሩ በድጋሚ አባል እንዲሆኑ በዕጩነት ቀርበዋል።
በጥብቅና እና በህግ ማማከር ስራ ላይ ያሉትና ከሰሞኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አባል ሆነው የተሾሙት አቶ በሻዳ ገመቹ ጉባዔውን እንደ አዲስ ተቀላቅለዋል።
አቶ በሻዳ ቀደም ባለው ጊዜ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት እና ፕሬዝዳንት ሆነው ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል።
“ሀበጋር” የተሰኘው የክርክር መድረክ መስራቹ አቶ ደበበ ኃይለገብርኤል፣ አቶ ቸርነት ዎርዶፋ፣ የፌደራል የፍትህ እና ህግ ኢንስቲትዩት የጥናት እና ምርምር ምክትል ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ማዳ እና አቶ አብደልአዚዝ አህመድ የጉባዔው አባላት እንዲሆኑ በዕጩነት ቀርበዋል።
የጉባኤው ዕጩ አባላት በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አማካኝነት እንዲሾሙ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አራት የፓርላማ አባላት የተቃወሙት ሲሆን አስራ ሁለቱ ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል።
በፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ አማካኝነት ይሾማሉ ተብለው የሚጠበቁት ስድስቱ የህግ ባለሙያዎች፤ የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ አባል ሆነው የሚቆዩት ለስድስት ዓመት ነው። የነባሩ ጉባኤ አባል የሆኑት የህግ ባለሙያዎች የተሾሙት ሰኔ 2007 ዓ.ም. ነበር።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሕግ አማካሪ የነበሩት ፋሲል ናሆም እና የቀድሞው የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሐሺም ቶፊቅም የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ አባላት ነበሩ።