የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ማይክ ሀማር ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አመራሮች ጋር ተወያዩ
ሀመር የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ ከአመራሮቹ ጋር መምከራቸው ተሰምቷል
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የአሜሪካ መንግስት ለስምምነቱ ምሉዕ ተፈጻሚነት ግፊት እንዲያደርግ ጠይቋል ተብሏል
የአሜሪካ የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ተወካይ ማይክ ሀመር ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋር በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙርያ መከሩ።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ እና ምክትል ፕሬዝዳንት ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ በውይይቱ ላይ መሳተፋቸው ተነግሯል፡፡
አቶ ጌታቸው በይፋዊ ማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ከሀመር ጋር የፕሪቶሪያው የዘላቂ ሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ በሚተገበርበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ለስምምነቱ ምልዑ ተግባራዊነት ግፊት እንዲያደርግ መጠየቃቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው፥ ማይክ ሀመር አሜሪካ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተልዕኮውን በፍጥነት እንዲወጣ ድጋፍ እንደምታደርግ መናገራቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በትግራይ ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ እና በሱዳን የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ አሜሪካ እና አጋሮቿ ድጋፍ እንዲያደርጉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም አሁን ያለው ሁኔታ ዘላቂ እንዳልሆነ እና የስምምነቱ ሙሉ በሙሉ አለመተግበር በአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል አፅንዖት ሰጥተው መናገራቸውን ነው የገለጹት፡፡
ከሳምንት በፊት የአሜሪካ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ማይክ ሀማር ከፈረንጆቹ መስከረም 3-13 ባለው ጊዜ ውስጥ ቤልጄየም፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መስርያ ቤት ባወጣው መግለጫ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
አሜሪካ የቀድሞ ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ፣ እንዲበተኑ እና ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ፣ ተፈናቃዮች በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ፣ የሽግግር ፍትህን እና ተጠያቂነትን በማጠናከር እና በሌሎች መንገዶች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የፌደራል መንግስቱን እና ህወሓትን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጻለች።
መግለጫው ከፕሪቶሪያው ስምምነት በተጨማሪም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት በሰላም በሚቋጭበት ሁኔታ ከባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ ብሏል።
ማይክ ሀመር ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሱዳን ጉዳይ ከኢጋድ እና ከአፍሪካ ህብረት ጋር ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ኃይሎች፣ በኦሮሚያ ክልል "ሸኔ" ተብሎ በሽብር ከተፈረጀው ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር ለአመታት፣ በአማራ ክልል ደግሞ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ከባለፈው አመት ሚያዝያ ጀምሮ የትጥቅ ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
በአማራ ክልል ያለውን ግጭት ለማስቆም መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ የጸጥታ ኃይል ያሰማራ ቢሆንም ግጭቱ አልቆመም።
በክልሉ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ እና ከግጭቱ አውድ ውጭ በርካታ ንጹሃን በዋናነት በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እየተገደሉ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን (ኢሰመኮ) ጨምሮ በርካታ አለምአቀፍ የመብት ተቆርቋሪ ተቋማት ሪፖርት ማውጣታቸው ይታወሳል።