ደብዳቤው በሱዳን መስኖ እና ውሃ ሃብት ሚኒስትር ለኢ/ር ስለሺ በቀለ የተጻፈ ነው
ሱዳን ከኢትዮጵያ ያገኘችውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ የተመለከተ የቴክኒክ መረጃን ተቃወመች፡፡
ካርቱም ትናንት ማክሰኞ ይህን ተቃውሞዋን ለኢትዮጵያ ማሳወቋን ገልጻለች፡፡
የመስኖ እና ውሃ ሃብት ሚኒስትሩ ያሲር አባስ (ፕ/ር) ለኢትዮጵያዊው አቻቸው ለኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የተቃውሞ ደብዳቤ መጻፋቸውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው አስታውቋል፡፡
ሚኒስትሩ የግድቡን ሁለተኛ ዙር ሙሌት በተመለከተ ባሳለፍነው ሃምሌ የሰጣችሁን ቴክኒካዊ መረጃ የተዛባ ነው ብለዋል፡፡
“የተዛባ እና ያልተሟላ መረጃን መስጠት የዓለም አቀፍ ህግጋትን መሰረታዊ መርሆዎች ይጥሳል ነው” ፕ/ር ያሲር አባስ በደብዳቤያቸው ያሉት፡፡
አባስ “በተዛቡ መረጃዎች እና በትብብር እጦት ምክንያት ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ተዳርገናል” ሲሉም ደብዳቤውን በግልባጭ ለአፍሪካ ህብረት እና ለአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ልከዋል፡፡
ሚኒስትሩ ኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በግድቡ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ሊያደርሱ የሚችሉ አፍሪካ ህብረት መር መፍትሔዎችን እንዲቀበሉም ነው ያሳሰቡት፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ይህ ዘገባ እስተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ተጻፈ የተባለውን ደብዳቤ በተመለከተ የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል እሳቤ እንዲደራደሩና የግድቡ ጉዳይ በአፍሪካ ህብረት በኩል እልባት እንዲያገኝ ደጋግማ ስትጠይቅ እንደነበር ይታወሳል፡፡
2ኛ ዙር ሙሌቱን የተመለከተ የቴክኒክ መረጃ “ሰጥተናል” በሚል ሲነገር እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ፕ/ር አባስም ቢሆኑም የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በሱዳን ላይ ያመጣው ተጽዕኖ እንደሌለ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
“በዘንድሮው ክረምት ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ የደረሰብን የጎርፍ አደጋ የለም” በማለትም ከጥቁር ዓባይ ይልቅ ነጭ ዓባይ ጎድቶናል ሲሉ መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡
የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ባሳለፍነው ሃምሌ መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡ የሙሌቱ መጠናቀቅ ከግድቡ ተርባይኖች ሁለቱ ኃይል እንዲያመነጩ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡
የዓባይ የታችኞቹ ተየፋሰስ ሀገራት የሆኑት ሱዳን እና ግብጽ ከግድቡ ሁለት የውሃ ማስተንፈሻዎች በዓመት 37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚያገኙ ኢ/ር ስለሺ መናገራቸውም የሚታወስ ነው።