ፕሮፌሰሩ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ባደረጓቸው ትንቅንቆች እና ፖለቲካዊ ትግሎችም ይታወቃሉ
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ማን ናቸው?
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ኢትዮጵያዊ ምሁር፣ፖለቲከኛ፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና ጸሃፊ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)ን ከመሰረቱ የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን መካከልም አንዱ ናቸው፡፡
ከአጼው ስርዓት ጀምሮ ንቁ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ያደርጉ የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን ላመኑበት ነገር ወደ ኋላ ሳይሉ ያለመታከት የሚታገሉ፣ አዋቂ፣ መካሪ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል፡፡
ቀስተ ደመና የተሰኘ ለዴሞክራሲና ማህበራዊ ፍትህ የቆመ ፓርቲ መስርተው በ1990ዎቹ መጨረሻ ግድም ያደረጉትን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴም ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ አይዘነጋም፡፡
ቅንጅት በሚል አንድ ጥላ ስር ተሰባበስበው ጉልህ እንቅስቃሴን በማድረጋቸው ለእስር ተዳርገው ከነበሩ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ልሂቃን መካከልም አንዱ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ነበሩ፡፡
የልጅነት ህይወት እና ትምህርት
ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ነው፡፡ 6 ኪሎ ይወለዱ እንጂ ሽሮ ሜዳ አድገዋል፤ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ህልፈተ ህይወታቸው እስከተሰማበት ጊዜም ድረስም በዚያው ኖረዋል፡፡
የልጅነት ጊዜያቸውን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ያሳለፉት ብላቴናው መስፍን እስከ ድቁና ለመድረስ ያስቻለ የቤተ ክህነት ትምህርትን ቀስመዋል፡፡
ነጻ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) አግኝተው ለተጨማሪ ትምህርት እ.ኤ.አ በ1951 ወደ እንግሊዝ ያቀኑ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከህንዱ ፑንጃብ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ እና የሶስተኛ ዲግሪያቸውን (MA and PhD) ከአሜሪካው ክላርክ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል፡፡
በኢትዮጵያ አጋጥሞ ከነበረው ድርቅ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ርሃብ መላው ዓለም እንዲያውቅና እንዲደግፍ ካደረጉት መካከል አንዱ እንደሆኑ የሚጠቀስላቸው ፕሮፌሰሩ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦግራፊ ፕሮፌሰር ነበሩ፡፡
ለተማሪዎቻቸው የሚሆን አጋዥ መጽሃፍን ካዘጋጁ ቀዳሚ የትምህርት ክፍሉ መምህራን መካከልም ይጠቀሳሉ፡፡
ከቢቢሲው ጆናታን ዲምቢልቢ ጋር በመሆን ድርቅና ርሃቡን ለአለም ያሳወቁት ፕሮፌሰሩ ሃገራቸውን በተለያዩ የኃላፊነት መስኮች አገልግለዋል።
ፖለቲካዊ ተሳትፎ
ጠንከር ባሉ ፖለቲካዊ ትችቶቻቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር መስፍን ገና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከነበሩባቸው ከ1950ዎቹ ጀምሮ ሲያደርጓቸው በነበሩ ፖለቲካዊ ተሳትፎዎች ይታወቃሉ፡፡
በታህሳሱ ግርግር እነ መንግስቱ ነዋይ የአጼ ኃይለስላሴን ዙፋን በነቀነቁበት ጊዜ ንቅናቄውን ከደገፉ የወቅቱ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች መካከልም አንዱ ነበሩ፡፡ ይህ ተሳትፏቸው በንገሱ ትዕዛዝ በወለጋ የጊምቢ አውራጃ አስተዳዳሪነት እስከመሾም አድርሷቸዋል፡፡ ሆኖም ፕሮፌሰሩ ሹመቱ በወቅቱ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸውን ሰዎች ከፖለቲካው ማዕከል ለማራቅ እና ዝም ለማሰኘት ነው በሚል ተቃውመዋል፡፡
በንጉሱ የአስተዳደር ዘመን ተፈጽመዋል የተባሉ ጥፋቶችን ለመመርመር በተቋቋመው መርማሪ ኮሚሽን ውስጥ ከተካተቱ እና በንጉሱ ፊት ቃለ መሃላ ከፈጸሙ 15 ኢትዮጵያውያን መካከልም አንዱ ነበሩ፡፡ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር በመሆንም አገልግለዋል፡፡
ወታደራዊው የደርግ ስርዓት ሃገሪቱን በተቆጣጠረበት ጊዜ ያሰራቸውን ከፍተኛ የንጉሱን ሹማምንቶች እንዲረሽን ይህ ከሚሽን ትልቅ ሚናን ተጫውቷል በሚል ይተቻል፡፡ ሆኖም ፕሮፌሰሩ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ይህን ጉዳይ አስተባብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ አብሮ ለመስራት ከደርግ የቀረበለትን ጥያቄ በወቅቱ ውድቅ ስለማድረጉም ነው የገለጹት፡፡
የትምህርት ተቋማት ከፖለቲካዊ ተጽዕኖዎች እንዲነጹ እና አካዳሚያዊ ነጻነት እንዲኖራቸው አበክረው ሲታገሉ እንደነበር የሚነገርላቸው ፕሮፌሰር መስፍን ከሌሎች የፖለቲካ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ቀስተ ደመና የተሰኘ ፓርቲን አቋቁመው ጉልህ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴን አድርገዋል፡፡
ቅንጅት በተሰኘ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረትን በመቀላቀል በ1997ቱ ምርጫ ያደረጉት ተሳትፎ ለእስር እስከ መዳረግ አድርሷቸው እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ላደረጉት አስተዋጽኦ በርካታ ሽልማቶችን ለመሸለም የበቁት ፕሮፌሰር መስፍን በተለያዩ ጋዜጦች እና ፍትህን በመሳሰሉት መጽሄቶች በሚጽፏቸው ጽሁፎች ይታወቃሉ፡፡
በቅርቡ ጽፈው ስለማጠናቀቃቸው ያሳወቁትን “ዛሬም እንደትናንት” መጽሃፍን ጨምሮ “እንዘጭ እምቦጭ”፣ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ”ን የመሳሰሉ 15 ገደማ መጽሃፍትን ለንባብ አብቅተዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ የሁለት ሴት ልጆች አባትም ናቸው፡፡
የፕሮፌሰሩን ህልፈተ ህይወት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም ከፕሮፌሰሩ ጋር የቀረበ ወዳጅነት እንዳላቸው የገለጹ አካላት ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለለውጧ ሲታገልላት የነበረን ታላቅ ሰው ማጣቷንም ጽፈዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ በፕሮፌሰሩ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ሃዘን በመግለጽ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡