“የኤርትራ ሹመቴ በዲፕሎማሲ ህይወት ውስጥ በድጋሚ ሊገኝ የማይችል ትልቅ ዕድል ነው”- ሬድዋን ሁሴን
“የጀመርኩትን ትምህርት አቋርጬ ነው ወደ አስመራ የሄድኩት”
“ሹመቱ ትልቅ ስሜትና ደስታ የመስጠቱን ያህል ስጋትም ነበረበት”
“የኤርትራ ሹመቴ በዲፕሎማሲ ህይወት ውስጥ በድጋሚ ሊገኝ የማይችል ትልቅ ዕድል ነው”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙበት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ለኢትዮጵያና ኤርትራ ዳግም ግንኙነት መጀመር ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ይጠቀሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ “ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባ እንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን፡፡ የበኩላችንንም እንወጣለን፡፡ በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ አገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለጽኩ፣ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ሲሉ ገልጸው ነበር፡፡
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም የሰማዕታት ቀን ሲከበር ወደ አዲስ አበባ ልዑክ እንደሚልኩ መግለጻቸው የቀጣናው ትልቅ ዜና ነበር፡፡
ይህንን ተከትሎም በመሪዎች በከፍተኛ የሃገራቱ ባለስልጣናትም ደረጃ ጉብኝት ጀመረ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሃምሌ 1 ቀን 2010 ዓ/ም የአስመራ ጉብኝትን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ አዲስ አበባ ወደ ሌሎችም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተመላለሱ፡፡
ይህንኑ ተከትሎም በሁለቱ ሃገራት መካከል ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ተጀመሩ፡፡ ኤምባሲዎች ተከፈቱ፤ አምባሳደሮችም ተሾሙ፡፡
ኢትዮጵያ የቀድሞውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሚኒስትር በኤርትራ አምባሳደር አድርጋ ስትሾም ኤርትራ ደግሞ ሰመረ ርዕሶምን በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር አድርጋ ሾመች፡፡
ከሹመቱ በፊት በተለያዩ የመንግስት ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ የነበሩት ሬድዋን አስመራ በገቡ በሦስተኛው ቀን ነበር የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳሌህ አቅርበው ሥራ የጀመሩት፡፡
አምባሳደር ሬድዋን የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሲያቀርቡ
አሁን ከኤርትራ ተመልሰው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ በኤርትራ የነበራቸውን ቆይታና የሹመታቸውን ሁኔታ በተመለከተ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
“አንድ በዲፕሎማሲ ውስጥ ያለሰው መልሶ ሊያገኘው የማይችል ዕድል ነው”
አሁን ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው እያገለገሉ ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ኢትጵያና ኤርትራ ወደ ጦርነት ሲያመሩ ሰራተኛ እንጂ ባለሥልጣን የገዢው ፓርቲ (ኢህአዴግ) አባልም አልነበሩም፡፡ ፓርቲውን በአባልና አመራርነት የተቀላቀሉትም በ1994 ዓ.ም ነበር፡፡ ኢትዮጵያን በኤርትራ እንዲወክሉ ሲሾሙም በአየር ላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡
አል ዐይን የሹመቱ ሁኔታ ምን እንደሚመስልና በወቅቱ ምን እንደተሰማቸው ላቀረበላቸው ጥያቄ “የዚህን ታሪካዊ ግንኙነት ሄደህ ማሳለጥ የምትመራበት ዕድል ማግኘት ከሁሉም አይነት ኃላፊነቶች የበለጠ ነው፤ ደስ የሚል ስሜት ይፈጥራል እና በከፍተኛ አመራሮቼ ወደ አስመራ ሄደህ አግዝ ስባል ሳላቅማማ ነው የሄድኩት፡፡ አርብ ተደውሎልኝ ሰኞ አዲስ አበባ መጥቻለሁ” ሲሉ መልሰዋል፡፡
“ጥሪው ታሪካዊ በመሆኑ” በወቅቱ ጀምረውት የነበረውን የሦስተኛ ድግሪ (Phd) ትምህርት አቋርጠው መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
“አንድ በዲፕሎማሲ ውስጥ ያለሰው ሊያገኘው የማይችል በብዙ ዓመታት አንድ ጊዜ ሊከሰት የሚችል በሀገርህ ሳይሆን ምናልባት በሌላ ሀገር ሊከሰት የሚችል ነገር ነው እኔ ጋር የመጣው እና በዚህ ረገድ ደስተኛ ነበርኩ ማለት ነው በደስታ ተቀብየ ነው የሄድኩት” ሲሉም ነው ዲፕሎማቱ በወቅቱ የነበረውን የሹመቱን ሁኔታ የሚያስታውሱት፡፡
“ሹመቱ ትልቅ ስሜትና ደስታ የመስጠቱን ያህል ስጋት ነበረበት”
አምባሳደሩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች እና የፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው በሰሩባቸው ጊዜያት ሁለቱ ሀገራት በበጎ አይተያዩም ነበር፡፡ በዐይነ ቁራኛም ነበር የሚተያዩት፡፡ ይህን ጉዳይ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዴት ሊያጣጥሙት እንደቻሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ
“የካቢኔ አባል የፓርቲ ኃላፊም ሆኜ እንደ ፖለቲካ የሚወሰደውን አቋምም የግሌን አቋምም፣ የግሌ ያልሆነ አቋምም መግለጽ ስለነበረብኝ ስገልጽ ቆይቻለሁ በዚህ ረገድ ሁሉንም ጠባሳ አውቀዋለሁ፡፡ እንደ ጓደኞቼ ሳስብ የሄዱት ጓደኞቼ ይናፍቁኛል፤ እንደ መንግስት ሳስብ የኢትዮጵያን አቋም ሳራምድ ቆይቻለሁ” የሚል ምላሽን ሰጥተዋል፡፡
ሹመቱ ትልቅ ስሜትና ደስታ የመስጠቱን ያህል ስጋት እንደነበረበት ግን አምባሳደሩ አልሸሸጉም፡፡
“20 ዓመት ሙሉ የተቋሰለን ነገር በመሪያችን የተለየ ስብዕና፣ የተለየ ድፍረት ምክንያት የመጣ ሰላም ነው እንጂ ያ ሁሉ መቋሰል እየተሟሸ እየተሟሸ የረገበ አልነበረም በዛኛው በኩል ግንኙነቱን በበጎ መቀበል ቢኖርም መሬት ላይ ሲወርዱ ምን ምን ነገሮች ሊከተሉ ይችላሉ በምን ያህል ፍጥነትስ ወደተሻለ መንገድ ያመጣል የሚለው ያሰጋ ነበር” ሲሉም ምክንያታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
የአየርላንድ ሹመታቸው
የአየርላንድ ሹመታቸውን በተመለከተ “ተገፍቼ ነበር የወጣሁት” ነው የሚሉት አምባሳደሩ፡፡
“ኢትዮጵያ ውስጥ የመስራት ፍላጎት አልነበረኝም፣ መማርም ቤተሰቦቼንም ማራቅ ስለነበረብኝ በወቅቱ ከነበሩት ኃላፊዎቼ ተደራድሬ፤ ሌላ የተሻለ ትልቅ ሀገር ተመድቤ አልፈልግም ብዬም ነበር የሄድኩት፡፡ ስለዚህ ቀለል ያለ ቦታ የፈለኩበት ከማንም ላለመነጋገርና ትምህርቴን ለመማር ነው” በሚልም ስለሁኔታው ይናገራሉ፡፡
የሃገራቱ ግንኙነትና ቀጣይ እጣ ፋንታ
በአስመራ ቆይታቸው ብዙ ለመስራት መሞከራቸውን የገለጹት አምባሳደሩ “የተበጣጠሰ ቤተሰብ ማገናኘት፤ ተለያይቶ የቆየን ዝምድና መቀጠል ብሎም ለመተጋገዝ የሚያስችል መንፈስን መፍጠር” እንደ ትልቅ ነገር መታየት እንዳለበት አብራርተዋል፡፡ ሰላም ከወረደ በኋላ መነጋገዱ፣ መንገድ መስራቱ፣ ወደብ መጠቀሙ ትርፍ እና በሂደት የሚመጡ ነገሮች ናቸው እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፡፡
“ከሁሉም በላይ የተፈጠረውን ጠባሳ ማከም ይቀድማል” የሚሉም ሲሆን ግንኙነቱን ተቋማዊ ለማድረግም እየተሰራ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡
ሆኖም ስራው በኢትዮጵያ በኩል ቢሄድ በሚባለው መልኩ እየሄደ አይደለም፡፡ ለዚህም ደግሞ በኤርትራ በኩል የሚሰጓቸው ምክንያች እንዳሉና አንዳንዶቹ በኢትዮጵያ በኩል የሚረዷቸው እንደሆኑ አንስተዋል፡፡ ጊዜ እየተሰጠ እና ቀስ እየተባለ ምክክር እየተካሄደ በነሱ ፍጥነት እና ዝግጁነት ልክ መሄድ ይገባልም ነው አምባሳደሩ የሚሉት፡፡
አምባሳደር ምህረተአብ ሙሉጌታም እርሳቸውን ተክተው በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደርነት ተሾመዋል፡፡
ከጦርነቱ በፊት በኢትዮጵያ የመጨረሻው የኤርትራ አምባሳደር የነበሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ግርማ አስመሮም ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡