በባንኮች ላይ የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች ሊጨምር እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ
ከ31 የኢትዮጵያ ባንኮች ላይ በ28ቱ ላይ የገንዘብ ማጭበርበር ተፈጽሟል ተብሏል
እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ የኢትዮጵያ ባንኮች 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ተጭበርብረዋል
በባንኮች ላይ የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች ሊጨምር እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ የገንዘብ ደህንነት ሪፖርቱን ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡ የባንኩ ሪፖርት እስከ ሰኔ 2024 ድረስ ባሉ የገንዘብ እንቅስቀሴዎች ዙሪያ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
ባንኩ በሪፖርቱ ላይ እንደጠቀሰው 28 የኢትዮጵያ ባንኮች 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በአጭበርባሪዎች ገንዘባቸውን አጥተዋል ብሏል፡፡
የማጭበርበር ድርጊቶቹ የተፈጸሙት በሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች፣ በተሰረቁ የኤትኤም ማሽኖች፣ በሐሰተኛ ቼኮች፣ በሐሰተኛ የስልክ መልዕክት እና ተያያዥ መንገዶች አማካኝነት ነው፡፡
በዚህ ዓመት ባንኮች ያጡት ገንዘብ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ300 ሚሊዮን ብር ጭማሪ እንዳሳየም በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ካሉ 31 ባንኮች ውስጥ 28ቱ ሲጭበረበሩ የቀሪዎቹ ሶስት ባንኮች ማንነት ግን በሪፖርቱ ላይ አልተጠቀሰም፡፡
ባንኮች ከአነስተኛ የብድር እና ቁጠባ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ብድሮችን እየሰጡ ነው የተባለ ሲሆን ይህ አገልግሎት እየጨመረ መሄድ እና የበይነ መረብ ማጭበርበሮች መበራከት ባንኮች የሚያጡት ገንዘብ ሊጨምር እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡