ብሔራዊ ሎተሪ የ16 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ እድለኛ እንደጠፋበት ገለጸ
እድለኛው ሰው እስከ የካቲት 30 ድረስ ካልመጣ ብሩ ለመንግሥት ገቢ ይደረጋል ተብሏል
ከሶስት ዓመት በፊት የ20 ሚሊዮን ብር እድለኛ ሽልማቱ ሊቃጠል አምስት ቀናት ሲቀሩት መጥቶ ብሩን መውሰዱ ይታወሳል
ብሔራዊ ሎተሪ የ16 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ እድለኛ እንደጠፋበት ገለጸ።
ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳድር በየጊዜው ለሽፓጭ ከሚያውላቸው የእድል ሎተሪዎች መካከል የእንቁጣጣሽ ሎተሪ አንዱ ነው።
20 ሚሊዮን ብር የሚያሸልመው ይህ እጣ ባሳለፍነው ጷግሜ 2015 ዓም እጣው የወጣ ሲሆን 1820259 ደግሞ የመጀመሪያ እድለኛ ቁጥር እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳድር ኮሙንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ቴድሮስ ንዋይ ለዓልዐይን እንዳሉት "ባሳለፍነው ጷግሜ ላይ የወጣው የእንቁጣጣሽ ሎተሪ አሸናፊ እስካሁን አልመጣም" ብለዋል።
ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳድሩ ይህን አሸናፊ እድለኛ እስከ ቀጣዩ የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ካልመጣ ወይም ካልመጣች ገንዘቡ ለመንግሥት ገቢ ይሆናልም ብለዋል።
20 ሚሊዮን ብር ከሚያሸልመው እጣ ቁጥር ውስጥ አንድ እጣ ያላው አንድ ሰው መጥቶ አራት ሚሊዮን ብሩን ወስዷል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ 16 ሚሊዮን ብር የሚያሸልም ሶት እጣዎች ያለው ወይም ያላት ሰው እስካሁን አልመጡም ሲሉም አክለዋል።
ሎተሪ እጣ ቆርጠው ቲኬቱን ደግመው እጣው ስለመውጣቱ እና አለመውጣቱን የማያረጋግጡ የሎተሪ ደንበኞች ስለሚኖሩ እጃቸው ላይ ያለውን ሎተሪ በድጋሚ እንዲያስተያዩም አቶ ቴድሮስ አሳስበዋል።
ከሶስት ዓመት በፊት አንድ የ20 ሚሊዮን ብር ሎተሪ ተሸላሚ ግለሰብ የሽልማት ጊዜው ሊያበቃ አምስት ቀናት ብቻ ሲቀረው መጥቶ እጁ ላይ በተገኘው ሶስት ሎተሪዎች መሰረት 16 ሚሊዮን ብሩን መውሰዱ ይታወሳል።
ሎተሪው ወጥቶ ሽልማታቸውን የማይወስዱ ሰዎች አጋጥሞ ያውቃል? በሚል ላነሳነው ጥያቄም " በተለይ አነስተኛ ሽልማት የሚያስገኙ እጣ የወጣላቸው ሰዎች የማይመጡበት እና ገንዘቡም ለመንግሥት ገቢ ይደረጋል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።
በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳድር ሕግ መሰረት እጣ የወጣላቸው እድለኞች እጃቸው ላይ ያለውን ሎተሪ ይዘው በስድስት ወራት ሽልማታቸውን መውሰድ የሚችሉ ሲሆን ስድስት ወራት ካለፈ ግን ገንዘቡ ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ ይደረጋል ይላል።