ተመድ በግድቡ ላይ ያወጣው መግለጫ“መርህን አክብራ ግድቧን እየገነባች ላለችው ኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነው”-የግድቡ ተደራዳሪ ዶ/ር ይልማ ስለሽ
ተመድ በግድቡ ላይ ያወጣው መግለጫ“መርህን አክብራ ግድቧን እየገነባች ላለችው ኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነው”-የግድቡ ተደራዳሪ ዶ/ር ይልማ ስለሽ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በትናንትናው ምሽት ያወጣው መግለጫ ለዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የመፍትሔ አቅጣጫ አቅርቧል፡፡በመግለጫው የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው ግድብ ዙሪያ፣ የግድቡ ባለቤት፣ግብጽና ሱዳን ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጠይቀዋል፡፡
ዋና ጸኃፊው ሶስቱ ሀገራት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላቸውን ልዩነት በፈረንጆቹ 2015 በሱዳን መዲና ካርቱም በተስማሙት ስምምነት መሰረት እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
ጥቁር ዓባይና ነጭ ዓባይን በምታገናኘው ካርቱም የተፈረመው ስምምነት “የመርሆዎች ስምምነት” የሚሰኝ ሲሆን በወቅቱ የሦስቱም ሀገራት መንግስታት መሪዎች ናቸው የፈረሙት፡፡
ስምምነቱን የፈረሙትም የቀድሞው ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽርና የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ናቸው፡፡
ይህ ስምምነት ለሶስቱም ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት በሚል የተፈረመ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ግን ግብጽ ሦስተኛ ወገን አደራዳሪ እንዲገባ ስትጠይቅ ቆይታለች፡፡
በዚህም መሰረት በፈረንጆቹ በ2019 አሜሪካና የዓለም ባንክ በግድቡ ላይ በተለይም በአዲስ አበባና ግብጽ በኩል ሥምምነት ላይ ያልተደረሰባቸውን ጉዳዮች ለመፍታት በአደራዳሪነት ቀርበው ነበር፡፡ ይሁንና የዋሸንግተንና የዓለም ባንክ የአደራዳሪነት ሚና ለአንድ ወገን አድልቷል የሚና ችግርም አለ በሚል ኢትዮጵያ የቤት ስራዬን መጨረስ እሻለሁ በማለቷ ከመጨረሻው የድርድር ሂደት መውጣቷ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ክረምት የግድቡን የመጀመሪያ ደረጃ የውኃ ሙሌት እንደምትጀመር መግለጿን ተከትሎ ግብጽ ጉዳዩን ከዋሸንግተን ኒውዮርክ ወደሚገኘው የጸጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች፡፡ ኢትዮጵያም በተመድ በወከለቻው አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በኩል ለግብጽ ምላሽ አስገብታለች፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች እንደሚሉት የአዲስ አበባ እና የካይሮ ወረቀቶች ኒውዮርክ ከገቡ በኋላ የተቋሙ ምላሽ ይጠበቅ ነበር፡፡
ተመድ ሶስቱ ሀገራቱ ካርቱም ጀምረውት የነበረውን የመርሆዎች ሥምምነት እንዲያከብሩት የሚገልጽ መግለጫ አውጥቷል፡፡ የድርጀቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባቸው ያለው የግድብ የድርድር ሂደት በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን አስታውቀዋል።
በእስካሁኑ የድርድሩ ሂደት መልካም ውጤቶች መገኘታቸውን የገለጹት ዋና ጸሃፊው ሶስቱ ሃገራት አሁንም በፈረንጆቹ 2015ቱ የስምምነት መርሆዎች የተቀመጡ የጋራ ተጠቃሚነት ስምምነቶችን ከዳር ለማድረስ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ይህንን ተከትሎ በ2015 የስምምነት ወቅት ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት የውኃ መሃንዲስ እና የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ይልማ ስለሽ (ዶ/ር) ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በካርቱም በተፈረመው የመርሆች ስምምነት መሰረት ስራዋን እየሰራች እንደሆነና የውኃ ሙሌቱንም በዛው መሰረት እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡
በዚህ ዓመትም ግድቡ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንዲይዝ በታቀደው መሰረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የግድቡን የውሃ ሙሌት መጀመሯ ዓለም አቀፍ ሕግ እንደሚፈቅድላት የገለጹት የውኃ መሐንድሱ ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀምን የሚከለክል ነገር የለም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በካርቱም የተፈረመውን የመርሆች ሥምምነት እንደምታከብር የገለጹት ዶ/ር ይልማ የመጀመሪያ ደረጃ የውኃ ሙሌትን ለመጀመር የማንም ፈቃድ አያስፈልግም የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡
በዚህም መሰረት በዚህ ዓመት 4 ነጥብ 9፣በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ 13 ነጥብ 5 እና በሦስተኛው ዓመት 10 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ ለመያዝ የታቀደ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህግንና የካርቱሙን የመርሆዎች ስምምነት ባከበረ መልኩ እንደምትከውን ነው የተደራዳሪ ቡድን አባሉ የገለጹት፡፡
እንደ ዶ/ር ይልማ ከሆነ የግደቡ ጉዳይ ከተመድ መድረሱና፣ ተመድ ካርቱም ተደርጎ የነበረው የመርሆች ስምምነትን ጠቅሶ ያወጣው መግለጫ መርህን አክብራ ግድቧን እየገነባች ላለችው ኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነው፡፡
ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ መርህ ተግባር ላይ እንዲውል ጠይቋል፤ ኢትዮጵያም መርህን ተከትላ የምትሰራ በመሆኑ ስራዋን የምታከናውነው በዚሁ መሰረት ይሆናል ብለዋል ዶ/ር ይልማ፡፡ ጉዳዩ በተመድ በኩል ይህንን ያህል ትኩረት ከማግኘቱም በላይ መርህ እንዲከበር መደረጉም ከኢትዮጵያ አቋም ጋር የተናበበ መሆኑን ዶ/ር ይልማ ገልጸዋል፡፡
የግድቡን መገንባት ስትደግፍ የነበረችው ሱዳን ኢትዮጵያ በመጭው ሀምሌ ወር ያቀደችውን የግድቡን የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት አልደግፍም የሚል አቋም አንጸባርቃለች፡፡ ግብጽ በአንጻሩ ከግድቡ የመሰረት ድንጋይ መጣል ጀምሮ የሚደርሰኝ የውሃ መጠን ይቀንሳል በማለት ተቃውሞዋን እያሰማች ቆይታለች፤ የግድቡን የውሃ ሙሌቱ እቅድንም አትቀበለውም፡፡