ዋትስአፕ በሙከራ ደረጃ የጀመረው “ኒውስሌተር” ምን የተለየ ነገር ይዞ መጥቷል?
የሜታ እህት ኩባንያ ዋትስአፕ ከዚህ ቀደም በኢሜል ይላኩ የነበሩ የምርትና አገልግሎት ማስታወቂያዎችን ተደራሽነት የሚለውጥ አገልግሎት በሙከራ ደረጃ ጀምሯል
በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚላኩ መልዕክቶች የመነበብ እድላቸው እስከ 98 በመቶ ይደርሳል
በየቀኑ ከ306 ቢሊየን በላይ የኢሜል መልዕክቶች ይላካሉ።
ይሁን እንጂ የተላኩት ሁሉ የመከፈት እድላቸው እየቀነሰ መሄዱን ጥናቶች ያሳያሉ።
በኢሜል የሚላኩ የተቋማት ማስታወቂያዎች የመከፈት እድላቸው ወደ 21 በመቶ መውረዱም ይነገራል።
ይህም ተቋማት ምርታቸውንም ሆነ አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ ከኢሜል ይልቅ ደንበኞቻቸው የሚያዘወትሯቸውን ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲያተኩሩባቸው አድርጓል።
- ዋትስአፕ ኢንተርኔት ቢቋረጥም ተጠቃሚዎች መልእክት እንዲላላኩ የሚያስችል አገልግሎት ሊጀምር ነው
- ዋትስአፕ በፈረንጆቹ በ2023 በየትኞቹ ስልኮች ላይ መስራት ያቆማል?
የማህበራዊ ትስስር ገጾችን የሚጠቀሙ ሰዎች በቀን ቢያንስ አንዴ መተግበሪያዎችን እንደሚከፍቱ ይታመናል፤ ይህም የተላከ መልዕክት የመከፈት ምጣኔውን 98 በመቶ እንዲደርስ ያደርገዋል።
ሰዎች ከተቋማት ጋር አንድ ለአንድ የሆነ ተግባቦትን እንደሚመርጡና በዚህ አይነቱ ግንኙነት የሚደረግ ግብይትም በደንበኞች ዘንድ አመኔታን መፍጠሩንም ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት።
እንደ ዋትስአፕ ያሉ ከ2 ቢሊየን በላይ እለታዊ ተጠቃሚ ያላቸው የማህበራዊ ትስስር ገጾችም ለዚህ ተመራጭ ናቸው።
የሜታ እህት ኩባንያ የሆነው ዋትስአፕ ተቋማት ለደንበኞቻቸው መልዕክት የሚልኩበትን አሰራር በይፋ ለመጀመር መዘጋጀቱን አስታውቋል።
የዋትስአፕ “ኒውስሌተር” የተቋማትን አዳዲስ ምርቶች እና ቅናሽ የተደረጋባቸው አገልግሎቶች ከተለመደው የኢሜል መልዕክት በተለየ መልኩ በምስል አስደግፎ መላክ የሚያስችል ነው ተብሏል።
ተቋማት ለደንበኞቻቸው በቀን ከአንድ በላይ መልዕክት መላክ ያለመቻላቸውም አስልቺነትን በማስቀረት ተደራሽነትን ያሰፋል ይላል ዘ ቨርጅ ድረገጽ ላይ የወጣው ዘገባ።
የመገናኛ ብዙሃንም በአንድ ጊዜ ለበርካታ ተከታዮቻቸው (ለእያንዳንዱ) ዜናዎችን እንዲልኩ የሚያስችል መሆኑን ተከትሎም ከፌስቡክና ትዊተር ባሻገር ፊታቸውን ወደ ዋትስአፕ እንደሚያዞሩ ይጠበቃል።
የዋትስአፕ አዲሱ አገልግሎት ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ግለሰቦች የራሳቸውን ቡድን ወይም ግሩፕ ያለምንም የቁጥር ገደብ በመፍጠር መረጃዎችን ማጋራትም ያስችላል ነው የተባለው።
ኩባንያው በቅርቡ የሚጀምረው “የኒውስሌተር” አገልግሎት እንደ ቴሌግራም ላሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ብርቱ ፉክክርን ይዞባቸው እንደሚመጣ ይጠበቃል።
በአለማችን ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን በላይ ደንበኞች ያሉት ዋትስአፕ በተለይ በሜታ ስር ከተጠቃለለ በኋላ ታማኝ መልዕክት መለዋወጫ ብቻ ሳይሆን ተዝናኖትን የሚፈጥሩና የኦንላይን ንግድን የሚያቀላጥፉ አሰራሮችን እየተገበረ ይገኛል።