ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ሰሜን ኮርያ እስከ 100 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን ወደ ሩስያ ልትልክ እንደምትችል መነገራቸው ይታወሳል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በዩክሬን ጦርነት ያለማቋረጥ ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል ገቡ፡፡
ባለፈው ወር ሰሜን ኮሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ወደ ሩሲያ ከላከች በኋላ በሁለቱ ሀገራት ትብብር መጠናከር ላይ አለም አቀፍ ስጋት እየጨመረ ባለበት ወቅት በመከላከያ ሚኒስትር አንድሬ ቤሎሶቭ የሚመራ የሩሲያ ወታደራዊ ልዑክ በትላንትናው እለት ሰሜን ኮሪያ ገብቷል።
ኪም እና ቤሎሶቭ ስልታዊ አጋርነትን ለማሳደግ ፣ ሉዓላዊነት ፣የደህንነት ፍላጎቶችን እና ዓለም አቀፍ ፍትህን በመጠበቅ ላይ የጋራ መግባባት መድረሳቸውን የሰሜን ኮርያ ቴሌቪዥን ኬሲኤንኤ ዘግቧል፡፡
በውይይቱ የሰሜን ኮርያው መሪ "ሩሲያ ሉዓላዊነቷን እና የግዛት አንድነቷን ከኢምፔሪያሊስቶች የበላይነት ለማስጠበቅ የምትከተለውን ፖሊሲ ሰሜን ኮርያ ሁልጊዜ ትደግፋለች" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሩስያው የመከላከያ ሚኒስትር ቤሉሶቭ ከሰሜን ኮሪያ አቻቸው ኖ ክዋንግ ቾል ጋር ተገናኝተዋል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች በነበራቸው ቆይታ የጋራ ጥቅም ለማሰጠበቅ በአለም አቀፍ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መቆም አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
እንደ አሜሪካ፣ ዩክሬን እና ደቡብ ኮሪያ ግምገማ፣ ሰሜን ኮሪያ ከ10ሺህ በላይ ወታደሮችን ወደ ሩሲያ የላከች ሲሆን አንዳንዶቹም በጦር ግንባር ላይ ውጊያ ማድረግ ጀምረዋል።
አሜሪካ ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ሌሎችም ሰሜን ኮሪያ የሩሲያ የጦር መሳሪያ ክምችት ለመሙላት የመድፍ ተተኳሾችን ሚሳኤሎችን እና ሌሎች መሳሪያዎችን እንደላከች ይናገራሉ።
ፒዮንግያንግም ሆነች ሞስኮ እስካሁን የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች እንቅስቃሴን በይፋ አላረጋገጡም የጦር መሳሪያ ድጋፍ ሪፖርቶችንም በፅኑ በማስተባበል ላይ ይገኛሉ፡፡
አሜሪካ እና አጋሮቿ ሩሲያ በምላሹ ለሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ሚሳኤሎችን ለመገንባት የሚያስችል ቴክኖሎጂን ሳትሰጥ እንደማትቀር ስጋት አላቸው፡፡
ባለፈው ሳምንት የደቡብ ኮሪያ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሺን ዎንሲክ ሩሲያ ለሰሜን ኮሪያ የአየር መቃወሚያ ሚሳኤል እንደሰጠች የደህንነት መረጃዎች አመላክተዋል ሲሉ ለሀገር ውስጥ ቴሌቪዥን ተናግረዋል ፡፡
በተጨማሪም ሩሲያ ለሰሜን ኮሪያ እና ለተለያዩ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች የገንዘብ ድጋፍ ማድረጓ የተገለጸ ሲሆን ድጋፉ በሳተላይት ቴክኖሎጂ እና የቅኝት ስርአቶች ላይ እንደሚያተኩሩ ኤፒ ዘገቧል፡፡