ሰሜን ኮሪያውያን ወላጆች ልጆቻቸው ከሩስያ ጦርነት ለማስቀረት የደመወዛቸውን መቶ እጥፍ ሀሰተኛ የህክምና ማስረጃዎችን እያሰሩ ነው ተባለ
የሳንባ ነቀርሳን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎች ለሚዘጋጅ ሀሰተኛ የህክምና ማስረጃ የሚከፈለው መቶ ዶላር ከ2024 መጨረሻ ጀምሮ በአምስት እጥፍ መጨመሩ ተገልጿል
በአለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በሰሜን ኮሪያ ከ100 ሺህ ሰዎች መካከል 513 ሰዎች በበሽታው ይያዛሉ
ሰሜን ኮሪያውያን ወላጆች ልጆቻቸው ከሩስያ ጦርነት ለማስቀረት የደመወዛቸውን መቶ እጥፍ ሀሰተኛ የህክምና ማስረጃዎችን እያሰሩ ነው ተባለ።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የኪም ጆንግ ኡን አገዛዝ 12 ሺህ ወታደሮችን ወደ ሩሲያ መላኩን እና በአሁኑ ወቅት በከርስክ ግዛት እየተዋጉ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም በመጪው ጊዜ ፒዮንግያንግ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ሩስያ የመላክ እቅድ እንዳላት የደቡብ ኮሪያ የደህንነት ተቋማት ተደጋጋሚ ሪፖርቶችን አውጥተዋል፡፡
በርካታ ቤተሰቦች ልጆቻቸው ወደ ሩሲያ እንዳይላኩ ለሆስፒታል ባለስልጣናት የውሸት የሳንባ ነቀርሳ የምስክር ወረቀት እና ሌሎች ሀሰተኛ የህክምና ማስረጃዎችን ለማሰራት የሚሰጡት ጉቦ ባለፈው አመት ከነበረበት 100 ዶላር በአምስት እጥፍ ጨምሯል።
በ2023 የአለም ጤና ድርጅት ሪፖርት መሰረት ሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ የሳንባ ነቀርሳ በሽታ ካለባቸው ሀገራት መካከል ያስቀመጣት ሲሆን ከ100 ሺህ ሰዎች መካከል 513 ሰዎች በበሽታው እንደሚያዙ አመላክቷል፡፡
ወላጆች ወደ ሩስያ ጦርነት የሚላኩ ልጆቻቸውን ድጋሚ የሚያዩበት እድል በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ በጥቁር ገበያ በተለያዩ ስራዎች የሚያገኙትን ገንዘብ ልጆቻቸውን ለማዳን እያዋሉት እንደሚገኙ ኒውስዊክ ዘግቧል፡፡
ዘገባው አክሎም የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር በሩስያ ጦርነት የሞቱ ወታደሮች በወታደራዊ ስልጠና ላይ እንደሞቱ የሚያስመስል ሰነድ በማዘጋጀት ለወላጆቻቸው እየላከ እንደሚገኝ ጠቅሷል፡፡
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልደሚር ዘለንስኪ እንዳሉት እስካሁን በከርስክ ግዛት 3800 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች መሞታቸውን ተናግረው ነበር፡፡
ሰሜን ኮሪያ በመንግስት ፖሊሲዎች እና በአለም አቀፍ ማዕቀቦች ምክንያት በከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ የምትገኝ ሀገር ብትሆንም 1.3 ሚሊዮን ሰራዊት በመያዝ በወታደር ቁጥር ከአለም በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ተጨማሪ 7.6 ሚሊዮን ወይም ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ህዝብ 30 በመቶ የሚሆነው ተጠባባቂ ጦር ሲሆን ይህም የሀገሪቱን ወታደራዊ አቅም ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑ ይታመናል፡፡
ይህን የሰራዊት አቅም ለማስቀጠል የሀገሪቱ መንግስት ወንዶች 10 አመት ሴቶች ደግሞ አምስት አመት እንዲያገለግሉ አስገዳጅ ህግ አውጥቷል፡፡