የሩሰያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት “የኒውክሌር አደጋዎች በአውሮፓም ሊከሰቱ ይችላሉ” አሉ
ዛፖሪዝሂያ ኃይል ማመንጫ በአውሮፓ ትልቁ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ መሆኑ ይታወቃል
ሜድቬዴቭ ሩሲያ በዩከሬነ የኒውክሌር ጣቢያው ላይ ጥቃት አድርሳለች የሚለውን የኪቭና አጋሮቿን ክስ አጣጥለዋል
የሩሲያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ፤ “የኒውክሌር አደጋዎች በአውሮፓም ሊከሰቱ ይችላሉ” ሲሉ አስጠነቀቁ፡፡
ሜድቬዴቭ ይህን ያሉት በዩክሬን ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ዙሪያ ኃይሎችን በማስፈር የኒውክሌር አደጋን በመፍጠር ሩሲያን ለሚወነጅሉት የዩክሬን አጋሮች ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
ሩሲያ እና ዩክሬን ከአውሮፓ ትልቅ የሆነውን እና በዩክሬን የሚገኘውን የዛፖሪዝሂያ ኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ ጥቃት በማድረስ እርስ በእርሳቸው በመካሰስ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
ሜድቬዴቭ ግን "እነሱ (ኪቭ እና አጋሮቿ) ሩሲያ ናት ይላሉ። ይህ በግልጽ 100 በመቶ ከንቱ ነው” ሲሉ በቴሌግራም ቻናላቸው ባጋሩት ጽሁፍ ተናግረዋል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ “የአውሮፓ ህብረት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎች እንዳሉትም መዘንጋት የለብንም፤ እናም እዚያ አደጋዎች ሊከሰቱ ይችላሉ” የሚል ማስጠንቀቅያ አዘል መልእክትም አስተላልፈዋል ሜድቬዴቭ።
በደቡብ ምስራቅ ዩክሬን የሚገኘው ዛፖሪዥያ አቶሚክ ሃይል ማመንጫ በአውሮፓ ትልቁና በዓለም ላይ ካሉት 10 ትላልቅ የኒውክሌር ኃይል ጣቢያዎች መካከል አንዱ ነው።
እናም በጦርነት ውስጥ የሚገኙትና እርስ በርስ የሚካሰሲት ሩሲያና ዩክሬን በጣቢያው ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከሀገራቱ በዘለለ ለተቀረው ዓለም ያልተፈለገ መዘዝ ይዞ እንዳይመጣ ተስግቷል።
ሁኔታው ያሰጋው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) በዩክሬን የኃይል ማመንጫ ጣቢያ አካባቢ የደረሰው ጥቃት በአካባቢ ከጦር ነጻ ቀጣና ይኑር የሚል ጥሪ ለማድረግ ተገዷል።
ተመድ ይህን ያለው በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር የዋለው የዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ጥቃት ድርሶበታል መባሉን ተከትሎ ነው።
ሁኔታውን ለመገምገም ሃሙስ እለት የተሰበሰው ተመድ፣ ሁለቱም አካላት የኃይል ጣቢያው አካባቢ ውጊያ እንዲያቆሙ ጠይቋል።
“ተቋሙ የወታደራዊ ዘመቻ አካል መሆን የለበትም፤ ይልቁንም የአከባቢውን ደህንነት ለማረጋገጥ ከወታደራዊ አንቅስቃሴ ነጻ ማድረግ ዙሪያ አስቸኳይ የቴክኒካል ደረጃ ስምምነት ያስፈልጋል” ሲልም ነው ተመድ በዋና ጸሃፊው ጉቴሬዝ ያሳሰቡት።
በስብሰባው ያላትን ስጋት የገለጸችው አሜሪካም፤ ቦታው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ እንዲሆንና ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ቦታውን እንዲጎበኝ አሳስባለች።