የዩክሬን ጦርነት “ክሬምያን ነጻ በማውጣት” መጠናቀቅ አለበት -ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ
ዘሌንስኪ ‘‘በክሬምያ የተጀመረው ጦርነት፤ ክሬምያን ነጻ በማውጣት መጠናቀቅ አለበት” ብለዋል
የዩክሬን አካል የነበረቸው ክሬምያ እንደፈረንጆቹ 2014 በተካሄደው ህዝበ ውሳኔን ወደ ሩሲያ መቀላቀሏ የሚታውስ ነው
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ፡የዩክሬን ጦርነት ክሬምያን ነጻ በማውጣት መጠናቀቅ አለበት አሉ፡፡
ዘለንስኪ በሰጡት መግለጫ ‘‘ክሬምያ ዩክሬናዊት ናት፤ አንተዋትም’’ ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
የዩክሬን አካል የነበረቸው ክሬምያ፤ እንደፈረንጆቹ 2014 የተካሄደውና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተቀባይነት ያላገኘው ህዝበ ውሳኔን ተከትሎ ወደ ሩሲያ መቀላቀሏ የሚታውስ ነው፡፡
በርካታ ዩክሬናውያን አሁን ላይ ከሩሲያ ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት የተጀመረው ያኔ ክሬምያ ወደ ሩሲያ ስትሄድ ነበር ብለውም ያምናሉ፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ በትናንትናው እለት በክሬምያ ሳኪ ተብሎ በሚታወቅ የሩሲያ ወታደራዊ ማዕከል ከባድ ፍንዳታ እንዳጋጠመ እየተነገረ ነው፡፡
ሩሲያ፤ ባይረጋገጥም ጥቃቱን የፈጸመችው ዩክሬን ከሆነች መዘዙ ከባደ ነው ስትል ማስጠንቅቋ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ስለ ፍንዳታው ከመናገር የተቆጠቡት ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ግን፤ አሁንም ክሬምያ ተመልሳ የዩክሬን ግዛት መሆኗ የማይቀር እንደሆነ በመዛት ላይ ናቸው፡፡
‘‘ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የተጀመረው በክሬምያ ነው፤ መጠናቀቅ ያለበትም በክሬምያ ነው….ነጻ ሆና’’ም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፡፡
ክሬምያን ወደ ዩክሬን የመመለስ ፍላጎት የሚያመላክተው የፕሬዝዳንቱ ንግግር፤ ከዚህ በፊት ይሉት ከነበረ የተለየ ይዘት ያለው እንደመሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ በወርሃ የካቲት 21 ቀን፤2022 በሰጡት መግለጫ ሩሲያ የተቆጣጠረቻቸው ግዛቶች ለቃ ከወጣች ዩክሬን ሰላም እንደምትቀበልና “ክሬምያ ቅድመ ሁኔታ እንደማትሆን” መግለጻቸው ይታወሳል፡፡