ሩሲያ የኒውክሌር ግጭት ስጋት ካለፉት አስርት ዓመታት ወዲህ ከፍ ብሏል አለች
ሞስኮ ዓለምን ከኒውክሌር ጦርነት ስጋት ለመጠበቅ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጻለች
ግንኙነታቸው እየሻከረ የመጣው አሜሪካ እና ሩሲያ በዓለም ላይ ታላላቅ የኒውክሌር ባለቤቶች ናቸው
ሩሲያ የኒውክሌር ግጭት ስጋት ካለፉት አስርት ዓመታት ወዲህ ከፍ ብሏል አለች።
የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ሪያብኮቭ እንደተናገሩት የኒውክሌር ግጭት ስጋት ካለፉት አስርት ዓመታት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሞስኮ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከዋሽንግተን ጋር ግልጽ የሆነ ግጭት ውስጥ ገብታለች ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አስጠንቅቀዋል።
ባለፈው ዓመት የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በሩሲያ እና በአሜሪካ መካከል ያለው የሻከረ ግንኙነት የበለጠ ተካሯል።
ባለፈው የካቲት ወር ሞስኮ ከዋሽንግተን ጋር የገባችውን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ቅነሳ ስምምነት ሰርዛለች።
ሮይተርስ ኢንተርፋክስ የዜና ወኪል ጠቅሶ እንደዘገበው ሰርጌ ሪያብኮቭ የኒውክሌር ግጭት ስጋት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።
“የኑክሌር ግጭት እድል ዛሬ ከፍተኛ ነው ወይ በሚለው ውይይት ውስጥ መዝለቅ አልፈልግም። ነገር ግን ካለፉት ጥቂት አስርተ ዓመታ ወዲህ ከፍ እያለ ነው ብለን እናስቀምጠው" ሲሉ ተናግረዋል።
ሪያብኮቭ ሩሲያ ዓለምን ከኒውክሌር ጦርነት ስጋት ለመጠበቅ ቁርጠኛ መሆኗንም ገልጸዋል።
ሞስኮ አሁን ከአሜሪካ ጋር ግልጽ የሆነ ግጭት ውስጥ መሆኗን በመግለጽ፤ ሁኔታዎች እንደተለመደው ሊቀጥሉ እንደማይችሉ ተናግረዋል።
በዩክሬን ጦርነት ክሬምሊን ዋሽንግተንን ለኪየቭ የጦር መሳሪያ በማቅረብ በግጭቱ ውስጥ በቀጥታ ተሳተፋለች በማለት ደጋግማ ከሳለች።
አሜሪካ እና ሩሲያ በዓለም ላይ ታላላቅ የኒውክሌር ኃያላን ሀገሮች ናቸው።
ሀገራቱ የኒውክሌር ጦርነት አሸናፊ እንደሌለው እና ፈጽሞ መዋጋት እንደማይገባ ቢናገሩም፤ በዩክሬን ያለው ግጭት ከምዕራቡ ዓለም ጋር ቀጥተኛ ጦርነት እንዳይፈጠር ስጋት ፈጥሯል።