በመላው ብሪታኒያ ያሉ ነርሶች በሚቀጥለው ወር የስራ ማቆም አድማ ሊያደርጉ ነው
በሮያል የነርስ ኮሌጅ በእንግሊዝ፣ ዌልስ፣ ሰሜናዊ አየርላንድ በደመወዝ ውዝግብ ምክንያት አድማ ሊመቱ ነው ብሏል
የሀገሪቱ መንግስት መደበኛ ድርድር ለማድረግ ማቅማማቱ ተነግሯል
በብሪታኒያ የሚገኙ ነርሶች ከመንግስት ጋር በተፈጠረ የደመወዝ ውዝግብ በሚቀጥለው ወር ከታህሳስ 15 እስከ 20 ድረስ የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ናቸው ተብሏል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት "የመደበኛ ድርድር አቋማችንን ውድቅ በማድረጉ በመላው እንግሊዝ፣ ሰሜን አየርላንድ እና ዌልስ የስራ ማቆም አድማው ይካሄዳል" ሲል የነርሶች ህብረት የሆነው የሮያል ነርሲንግ ኮሌጅ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ከገና በዓል በፊት የሚካሄደው የስራ ማቆም አድማ የመጀመሪያ እርምጃቸው እንደሚሆን የገለጸው ህብረቱ "መንግስት ወደ መደበኛ ድርድር ካልገባ በታህሳስ ወር ተጨማሪ የስራ ማቆም አድማ ቀናት ሊቀጥሉ ይችላሉ" ብሏል።
ነገር ግን መንግስት መደበኛ ድርድር ከማድረግ ተቆጥቧል ተብሏል።
"በየትኛውም ጊዜ አድማዎችን የማስቆም ኃይል እና ዘዴ አላቸው ነገር ግን በዚህ መንገድ መሄድን መርጠዋል" ሲል መንግስትን ወቅሷል።
አለመግባባቱ ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን በታካሚዎች ደህንነት ጭምር ላይም መሆኑን የገለጸው ህብረቱ "የሰራተኞች ደረጃ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ለታካሚዎች እንክብካቤም በዚሁ ልክ ነው ብሏል። ለነርስ ሰራተኞች ፍትሃዊ ክፍያ ስንከፍል ብቻ በሙያችን ሰዎችን ቀጥረን እናቆያለንም ብሏል።
"እስካሁን ከዩናይትድ ኪንግደም መንግስት ጋር ባደረግነው ስብሰባ ሚንስትሮች የብሄራዊ ጤና አገልግሎት ክፍያ እና የታካሚ ደህንነትን አሳሳቢ ጉዳዮች ወደ ጎን ሲያደርጉ አይተናል" ሲል ህብረቱ በመግለጫው ገልጿል።
የሮያል ኮሌጅ ዋና ጸሃፊና ስራ አስፈፃሚ ፓት ኩለን "አባሎቻችን እንዲህ አይነት ኢ-ፍትሃዊነት እንደተሰማቸው ካረጋገጥን በኋላ መንግስት አድማ እንደምንመታ ካወቀ ከሁለት ሳምንት በላይ አልፏል” ብለዋል።
"የነርስ ሰራተኞች ለታካሚዎች የሚገባቸውን እንክብካቤ መስጠት አለመቻላቸው፣ ዝቅተኛ ክፍያ እና ደህንነቱ ያልተጠበቀ የሰው ሃይል ደረጃ ሊበቃ ይገባል" ሲሉ ኩለን ተናግረዋል።
ብሪታንያ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እና ምጣኔ-ሀብቱ እያሽቆለቆለ ባመጣው የኑሮ ውድነት ቀውስ የተቀሰቀሰ የሰራተኛ ማዕበል አጋጥሟታል ሲል አናዶሉ ዘግቧል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የባቡር፣ የባህር እና የምድር የትራንስፖርት ሰራተኞች ማህበር ለገና በዓል እና ለአዲሱ ዓመት ተከታታይ የ48 ሰአታት የባቡር አድማ እንደሚመታ አስታውቋል።