ሞ ፋራህ፤ ታዳጊ እያለ በአንዲት በማያውቃት ሴት ተገዶ ብሪታንያ መግባቱን ተናገረ
በስደተኛነት ብሪታኒያ እንዳልገባና ወላጆቹ ብሪታኒያን ረግጠው እንደማያውቁም ነው ፋራህ የተናገረው
አትሌቱ ትክክለኛ መጠሪያው ሞ ፋራህ እንዳይደለም ተናግሯል
ሞ ፋራህ ታዳጊ እያለ በአንዲት በማያውቃት ሴት ተገዶ ከጅቡቲ ወደ ብሪታንያ በህገ ወጥ መንገድ መግባቱን ተናገረ፡፡
የኦሎምፒክ ሻምፒኑ ትክክለኛ መጠሪያ ስሙ ሞ ፋራህ እንዳይደለና ትክክለኛ ስሙ ሁሴን አብዲ ካሂን እንደሆነ ከቢቢሲ ዶክመንታሪ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል፡፡
እንደ አትሌቱ ገለጻ ከሆነ ገና የ8 ወይ የ9 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነው በአንዲት አይቷት እንኳን በማያውቅ ሴት አስገዳጅነት ከጅቡቲ ወደ ብሪታኒያ የገባው፡፡
መሀመድ ፋራህ የሚል ስም ተሰጥቶት ወደ ብሪታኒያ እንዲገባና ባመጣችው ሴት ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ልጆችን እንዲንከባከብ መደረጉንም ነገ ረቡዕ ይታያል ለተባለውና "እውነተኛው ሞ ፋራህ" በሚል ለተዘጋጀው የቢቢሲ ቲቪ ዘጋቢ ፊልም ተናግሯል ።
የሎንደን እና የሪዮ ኦሎምፒኮች የ5 ሺ እና የ10 ሺ ርቀቶች ሻምፒዮናው ሞ ከአሁን ቀደም ከወላጆቹ ጋር ከሶማሊያ ወደ ብሪታኒያ የገባ ስደተኛ እንደሆነ ነበር የሚናገረው፡፡ ሆኖም አሁን ወላጆቹ ብሪታኒያን ረግጠው እንደማያውቁ ተናግሯል፡፡
የ39 ዓመቱ እውቅ አትሌት ገና የ4 ዓመት ታዳጊ ሳለ ወላጅ አባቱ በሶማሊያ ተቀስቅሶ በነበረ ግጭት እንደተገደለና ወላጅ እናቱን ጨምሮ ሁለት ወንድሞቹ ደግሞ በሶማሊ ላንድ እንደሚኖሩም ነው በዘጋቢ ፊልሙ የተናገረው፡፡
"እውነታው እንደምታስቡት እኔ ሞ ፋራህ አይደለሁም" የሚለው አትሌቱ እውነተኛ ስሙ "ወደ ዘመዶችህ እየወሰድኩህ ነው" ባለችውና መሐመድ ፋራህ በሚል ስም ሃሰተኛ ሰነዶችን ባዘጋጀችው በሴትዮዋ እንደተቀየረ እና ትክክለኛ ስሙም ሁሴን አብዲ ካሂን እንደሆነ ገልጿል፡፡
የአራት ጊዜ የኦሎምፒክ ወርቅ ሻምፒዮናው ፋራህ ይህን ለዓመታት አምቆት የኖረውን እውነታ በልጆቹ እና በባለቤቱ ግፊት አደባባይ ለማውጣት መድፈሩን ተናግሯል በዘጋቢ ፊልሙ፡፡
ውስጥ ውስጡን ከመብሰልሰልና በልጆቹ ሲጠየቅ ምላሽ ከማጣት ለመውጣትም በማሰብ እንደተናገረውም ገልጿል ፋራህ፡፡
ፋራህ ብሪታኒያ በደረሰ ጊዜ ህይወት በተነገረው ልክ ሆና አልጠበቀችውም፡፡ በህገ ወጥ መንገድ ይዛው የመጣችውም ሴትዮ ያዘጋጀቻቸውን የጉዞና ሌሎችንም ትክክለኛ ማንነቱን የሚያሳዩ ሰነዶችን ቀዳዳ ጥላለች፡፡
በዚያ ችግር ላይ መውደቁ እንደማይቀር መረዳቱን የሚናገረው ፋራህ ራሱን ለማኖር ሲል ህጻናትን መንከባከብን ጨምሮ ሌሎች የጉልበትና የቤት ስራዎችን መስራት ተገዶ ጀመረ፡፡ ብዙ ጊዜ መታጠቢያ ክፍል እየገባ ያለቅስ እንደነበርም ነው የሚያስታውሰው፡፡
ሆኖም ታዳጊው መሮጥ ሲጀምር እንዴት እንደሚቀየር አይተው በአትሌቲክሱ እንዲገፋ ላበረታቱት የሰውነት ማጎልመሻ መምህሩ አለን ዋትኪንሰን ገለታ ይግባና ከነበረበት ችግር ሊወጣና በእርሳቸው እውነታውን ነጋሪነት በፈረንጆቹ ሚሊኒዬም ዜግነት ሊያገኝ መቻሉን ይናገራል፡፡
ሆኖም ስለዚያ እድሉን ቀምቶት ብሪታኒያ እንደገባ ስለሚያስበው ልጅ ስለ ትክክለኛው ሞሃመድ ፋራህ ማሰብ መብሰልሰሉ አልቀረም፡፡ ደህና ይሆናል የሚል ግምት እንዳለውም ተናግሯል፡፡
እውነታውን በመናገሩ እየተደነቀ ያለው ሞ የሱን መሰል ልብ የሚነኩ የስደት ታሪኮች እንዳሉ በማስታወስ ጥገኝነት ለሚፈልጉ ስደተኞች ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይገባል ብሏል፡፡
ስደተኞችን በተሻለ ሁኔታ ለመያዝ ቃል የገባችው ብሪታኒያ በቅርቡ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በሩዋንዳ አሰፍራለሁ የሚል እንቅስቃሴ መጀመሯ ይታወሳል፡፡