“የበቴ ኡርጌሳን ግድያ በመንግስት አካላት እንደተፈጸመ ተደርጎ እየተናፈሰ ያለው መረጃ ተቀባይነት የለውም” የኦሮሚያ ክልል መንግስት
የኦሮሚያ ክልል መንግስት የበቴ ኡርጌሳን ግድያ ዘውግዞ መግለጫ አውጥቷል
በቴ ኡርጌሳ እስካሁን ማንነታቸው ባልታወቀ አካላት በመቂ ከተማ መገደላቸውን የክልሉ መንግስት አስታውቋል
የኦሮሚያ ክልል መንግስት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳን ግድያ በመንግስት አካላት እንደተፈጸመ ተደርጎ እየተናፈሰ ያለው መረጃ ተቀባይነት እንደሌለው አስታወቀ።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ በትውልድ ስፍራቸው መቂ ከተማ በጥይት ተመተው መገደላቸው መገለጹ ይታወቃል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙየኒኬሽን ቢሮ ይህንን ተከትሎ ትናንት ምሽት ባወጣው መግልጫ፤ የኦነግ አባል በነበሩት አቶ በቴ ኡርጌሳ ላይ የተፈጸመው ግድያ እንዲሁም ግድያውን መንግስት ላይ ለማላከክ የሚደረገው ጥረት በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የለውም ብሏል።
የክልሉ መንግስት በመግለጫው፤ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ላይ የተፈጸመውን ግድ አውግዟል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባል ከመንግስት ጋር የፖለቲካ አቋመ ልዩነት ስላለው ብቻ የግድያው በመንግስት አካል እንደተፈጸመ ተደርጎ እየተናፈሰ ያለው ፕሮፖጋንዳ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነተ የሌለው መሆኑንም የክልሉ መንግስት በጥብቅ አስታውቋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት አክሎም የኦነግ አባሉ በቴ ኡርጌሳ እስካሁን ማንነቱ ባልታወቀ አካል በመቂ ከተማ ተገድለው መገኘታቸውን በመግለጫው አመላክቷል።
የክልሉ መንግስት በአቶ በቴ ኡርጌሳ ላይ የተፈጸመውን የግድያ ወንጀል የህግ የምርመራ ሂደቶችን ተከትሎ ለህዝቡ ይፋ የሚያደርግ መሆኑንም አስታውቋል።
የፀጥታ አካላት በምርመራ እስከሚያረጋግጡ ድረስ የግድያ ተግባሩን ኃላፊነት ለየትኛውም አካል መስጠት እንደማይቻል ያሳሰበው የኦሮሚያ ክልል መንግስት፤ የትኛውም አካል በማስረጃ ያልተረጋገጠ ፕሮፖጋንዳዎችን ከመንዛት እንዲቆጠብም አስጠንቅቋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(አነግ) ባወጣው መግለጫ አባለቱ አቶ በቴ ኡርጌሳ በትውልድ ከተማው መቂ መገደሉን አገኘሁት ባለው መረጃ ማረጋገጡን ገልጿል።
ኦነግ በመግለጫው በአባሉ በቴ ኡርጌሳ ላይ የደረሰው "ዘግናኝ ግድያ" በገለልተኛ አካል እንዲመረመር ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የኦሮሚያ ክልል እና የፌደራል ባለስልጣናት "ፈጣን፣ገለልተኛ እና ሙሉ" ምርመራ አድርገው ግድያውን የፈጸሙትን ተጠያቂ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።