የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ፋርማጆ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብል “የዘገየውን ምርጫ” ለማካሄድ ተስማሙ
መሪዎቹ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት የታችኛው ምክርቤት /ፓርላማ/ ምርጫ ይካሄዳል" ብለዋል
አሁን ከስምምነት የደረሱት ፕሬዝዳንት ፋርማጆ እና ጠቅላይ ሚኒሰትር ሮብል ከቅርብ ጊዜት ወዲህ በከፋ ቅራኔ ውስጥ ገብተው እንደቆዩ ይታወቃል
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒሰትር የአፍሪካ ቀንዷ ሀገረ ሶማሊያን እንደገና ወደ ቀውስ ይዳርጋታል ተብሎ የተሰጋውንና በመካከላቸው የነበረው ፍጥጫ ወደ ጎን በመተው “የዘገየውን የሀገሪቱ ምርጫ” ለማካሄድ ከስምምነት መድረሳቸው አስታወቁ፡፡
ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ/ፎርማጆ/ እና ጠቅላይ ሚኒሰትር ሞሃመድ ሁሴን ሮብል በትናንታነው ዕለት በሰጡት መግለጫ" አመራሩ በስማማው መሰረት ሁሉንም የፌዴራል መንግስታት በቀጣይ ሁለት ሳምንታት የታችኛው ምክርቤት /ፓርላማ/ ምርጫ እንዲያካሂዱ ጥሪ አቅርቧል" ብለዋል፡፡
ቀጣዩ ዙር ደግሞ ከጥቅምት 1 እስከ ህዳር 25/2021 እንደሚካሄድ ነው የገለጹት መሪዎቹ፡፡ በሶማሊያ የሚደረጉ ምርጫዎች በተዘዋዋሪ የተወሳሰበ ሞዴል (a complex indirect model ) የሚከተሉ ናቸው፡፡
በዚህም የክልል ምክር ቤቶች እና የጎሳ ተወካዮች ለብሔራዊ ፓርላማ የሕግ አውጭዎችን ይመርጣሉ ፣ እነሱ ደግሞ ፕሬዝዳንቱን የሚመርጡ ይሆናል።አሁን ከስምምነት የደረሱት የሶማሊያ መሪዎች ከቅርብ ጊዜት ወዲህ በከፋ ቅራኔ ውስጥ ገብተው እንደቆዩ ይታወቃል፡፡
በተለይም የሀገሪቱ ደህንነት ባልደረባ የነበረችው ኢክራም ታህሊል ደብዛ መጥፋት ጋር በተያያዘ ሮብል የሀገሪቱን የደህነት ሹም ፋሃድ ያሲን ሀጂ ጣሂርን ከሃላፊነት ማስነሳታቸው ይበልጥ አቃቅሯቸዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒሰትሩ እርምጃ ተክትሎም ፋርማጆ ፋሃድ ያሲን ሀጂ ጣሂርን ከስልጣን መነሳት በመቃወም የብሔራዊ ደህንነት አማካሪያቸው አድርገውም ሾመዋል፡፡
ይህ ቅራኔያቸው ተባብሶም ፋርማጆ ሮብል “ከስልጣኑ እያለፈ ነው” በሚል የስልጣን ገደብ አደረጉ፡፡ሮብል ሃገራዊ ምርጫው እስኪጠናቅቅ ድረስ ፕሬዝዳንቱ ባለሥልጣናትን የማስወገድም ሆነ የመሾም ሥልጣን እንደሌላቸውም መግለጫ አወጡ።
የመሪዎቹ ሽኩቻ ተክቶም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና አፍሪካ ህብረት ጉዳዩ እንዲያረግቡት እና ለአፍሪካ ቀንዷ ሀገረ ሶማሊያ የሚበጅ መንገድ እንዲመርጡ ሲማጸኑ ቆይቷል፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ የሶማሊያ መሪዎች ወደ ስምምነት መምጣቻውም ታድያ፤ ዳግም ወደ ቀውስ እንዳትገባ በዓለም አቀፉ ማህበረስብም ሆነ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንዳ ስጋት ውስጥ ገብታ ለነበረችው ሶማሊያ ትልቅ ተስፋ ነው ተብሎለታል፡፡