በዩክሬን ሉሃስክ ክልል የሚገኙ 284 ሺህ ነዋሪዎች የሩሲያ ዜግነት መቀበላቸው ተገለፀ
ሩሲያ በያዘቻቸው የዩክሬን ከተሞች ፓስፖርት መስጠት መጀመሯ ይታወቃል
ዩክሬን “ሩሲያ እያደረገችው ያለው ተግባር በግዛቴ ውስጥ የሩሲያ ዜጎች መፈጠር ነው” ብላለች
በዩክሬኗ ሉሃንስክ ግዛት ውስጥ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የሩሲያን ዜግነት መቀበላቸው ተገለፀ።
እስካሁን ባለው ጊዜም ከ284 ሺህ በላይ ሉሃንስክ ግዛት ነዋሪዎች ዜግነታቸውን ወደ ሩሲያ መቀየራቸውን ታስ የዜና ተቋምን በመጥቀስ ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
በአሁኑ ወቅትም የሩሲያን ዜግነት ለመቀበል የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱ የሉሃንስክ ክልል አስተዳዳሪ ሊዮኒድ ፔስችኒክ ተናግረዋል።
ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው የዩክሬን አካባቢዎች ከሳላፍነው ቅዳሜ ጀምሮ የዜግነት ፓስፖረት መስጠት መጀመሯ ይታወሳል።
የሩሲያን ፓስፖርት መስጠት የተጀመረው በኬርሶንና ማሪፑል ከተሞች ሲሆን፤ በመጀመሪያው ቀንም፤23 የኬርሶን ከተማ ነዋሪዎች የሩሲያን ፓስፖርት መቀበላቸውን ታስ አስነብቧል።
የሩሲያ ፓስፖርት ለመውሰድም በኬርሶንና ማሪፑል ከተሞች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ማመልከታቸውም እየተነገረ ይገኛል።
ዩክሬንበበኩሏ “ሩሲያ እያደረገችው ያለው ተግባር በግዛቴ ውስጥ የሩሲያ ዜጎች መፈጠር ነው” በማለት ማውገዟም ተስመቷል።
ሩሲያ በዩክሬን ግዛት ውስጥ ፓስፖርት መስጠት መጀመሯ የዩክሬንን የግዛት እንደነት የሚፈታተን እና ዓለም አቀፍ ህጎችን የጣሰ መሆኑንም አስታውቃለች።
በቅርቡም የመጀመሪያው የሩሲያ ባንክ በሩብል መገበያየትና የሩሲያን የቴሌኮምና ሌሎችንም አገልግሎቶች መጠቀም በጀመረው የኬርሶን አካባቢ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር የአካባቢው የአስተዳደር አካላት ማስታወቃቸው ይታወሳል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዘመናዊቷ ሩሲያ ዕጣ ፋንታ የሚወሰነው የቀድሞ ግዛቶቿን መመለስና ማጠናከር መሆኑን ማስታወቃቸውም አይዘነጋም።