ምዕራባውያን ሩሲያን ለመውረር እየተዘጋጁ እንደነበር ፕሬዝዳንት ፑቲን ገለጹ
የሩሲያ ጦር በዩክሬን እያካሄደው ያለው ልዩ ዘመቻ የዚሁ አካል ነውም ብለዋል
ወረራው ሊፈጸም ዝግጅት የነበረው በዩክሬን በኩል እንደነበርም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል
ምዕራባዊያን ሩሲያን ለመውረር እየተዘጋጁ እንደነበር ፕሬዝዳንት ፑቲን ገለጹ፡፡
ሩሲያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመን የሚመራውን ጥምር ጦር ያሸነፈችበትን 77ኛ ዓመት የድል ቀን በዓል ዛሬ ሰኞ አክብራለች፡፡
የድል ቀኑን አስመልክቶ 11 ሺህ በላይ የሩሲያ ወታደሮችወታደራዊ ትርዒቶችን ያቀረቡ ሲሆን፤ የሩሲያ አየር ኃይልም የተለያዩ የአየር ላይ ትርዒቶችን አሳይቷል።
በድል በዓሉ የአከባበር ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያን በዩክሬን በኩል አድርገው ሩሲያን ለመውረር እየተዘጋጁ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ሆኖም የሩሲያ ጦር የወረራ እቅዱን በመመከት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፤ ልዩ ዘመቻ እንዲካሄድ መወሰናቸው ትክክል እንደነበር የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፡፡
እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ያሉት ልዩ ዘመቻ እንዲካሄድ በትክክለኛው ሰዓት ትክክለኛ ውሳኔ እንደተደረገም ፕሬዝዳንት ፑቲን በስነ ስርዓቱ ተናግረዋል፡፡
“በራሪው ታንክ” የሚል መጠሪያ ያለው የሩሲያ ሄሊኮፕተር
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶ ዶምባስ ከተባለው የዩክሬን ግዛት በጎፈቃደኞችን በመመልመል ጥቃት የመክፈትና የሃገራቸውን ታሪክ የማጥፋት እቅድ እንደነበረው የተናገሩት ፑቲን የሩሲያ ጦር ለእናት ሀገሩ እየተፋለመ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ሩሲያ በዶንባስ የሚገኙት ዶኔስክ እና ሉሃንስክ አካባቢዎች ሪፐብሊክ መሆናቸውን አውጃለች፡፡ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ከሩሲያ የሚመዘዝ ዘር እንዳላቸው ይነገራል፡፡ ክሬሚያን በግዛትነት የጠቀለለችው ሩሲያ ረጅም ዓመታትን በጭቆና ማሳለፋቸውን በመጥቀስም ነበር ልዩ ወዳለችው ዘመቻ የገባችው፡፡
የሃገርን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ነው በተባለለት በልዩ ዘመቻ የተሳተፉ ሩሲያውያንን ቤተሰቦች እንደሚደግፉ የጠቆሙት ፕሬዝዳንት ፑቲን ጦራቸው የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቹን ዝግጁ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ልዩ ዘመቻ ማካሄድ ከጀመረች 75 ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ዘመቻውን ተከትሎ ከ6 ሺህ በላይ ማዕቀቦች በምዕራባውያን ሃገራትና አጋሮቻቸው የተጣሉባትም የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ትገኛለች፡፡
በጦርነቱ 12 ሚሊዮን ገደማ ዩክሬናውያን የመኖሪያ ቀያቸውን ለቀው ለስደት መዳረጋቸው ይነገራል፡፡