ኮሮናን በውጤታማነት ለመከላከል የቻለ ክትባት ማዘጋጀቱን ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ
በሁለት የተለያዩ መንገዶች ካደረገው ፍተሻ በአንደኛው 90 በመቶ ያህል የተረጋገጠ ውጤት ማግኘቱንም ነው ዩኒቨርስቲ የገለጸው
ክትባቱ በአስር የተለያዩ ሃገራት በስፋት እየተመረተ እንደሚገኝም አስታውቋል
ኮሮናን በውጤታማነት ለመከላከል የቻለ ክትባት ማዘጋጀቱን ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ
ከአስትራዜናካ ጋር በመቀናጀት በኮሮና ቫይረስ ክትባቶች ላይ ሲያደርግ በነበረው ሙከራ ተስፋ ሰጪ ውጤት ማግኘቱን ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ፡፡
ዩኒቨርስቲው ChAdOx1 nCoV-2019 ሲል በሰየመው ክትባቱ ላይ በሁለት የተለያዩ መንገዶች በተደረገ የምዕራፍ ሶስት ፍተሻ 70.4 በመቶ ያህል አማካይ ውጤት ማስገኘቱንም በድረገጹ ያሰፈረው መረጃ ያሳያል፡፡
አንደኛው የፍተሻ መንገድ 90 በመቶ ሁለተኛው ደግሞ 62 በመቶ የተረጋገጠ ውጤት ማስገኘታቸውንም ነው ዩኒቨርስቲው የገለጸው፡፡
ይህ ብዙዎችን ሊታደግ የሚችል ግኝት ነው ብለዋል በጎ ፍቃደኞችን ያመሰገኑት የክትባት አዘጋጁ የተመራማሪዎች ቡድን አስተባባሪ ፕሮፌሰር አንድሩ ፖላርድ፡፡
በክትባቱ የዝግጅት ሂደት እንግሊዝን ጨምሮ በደቡብ አፍሪካ እና ብራዚል የሚገኙ ከ24 ሺ በላይ በጎ ፍቃደኞች ተሳትፈዋል፡፡
ክትባቱ በየሃገራቱ ባሉ የጤና ተቋማት በቀላሉ ሊሰጥ ይችላል ተብሎለታል፡፡
በአስር የተለያዩ ሃገራት በስፋት እየተመረተ እንደሚገኝም ነው የተገጸው፡፡
በክትባቶቹ ውጤታማነት መደነቃቸውን የገለጹት የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ቀሪ የሙከራ ሂደቶች ቢኖሩም ግኝቱ ሊደነቅ የሚገባው ነው ብለዋል፡፡
ተመራማሪዎቹንና በጎ ፈቃደኞቹንም አመስግነዋል፡፡