የየመን ተፋላሚ ወገኖች ረመዳንን ታሳቢ አድርገው ተኩስ ለማቆም ተስማሙ
በየመን የሚንቀሳቀሱት የሃውሲ አማጽያን በቅርቡ በሳዑዲ እና በዩኤኢ ጥቃት መፈጸማቸው ይታወሳል
የረመዳን የጾም ወራትን ታሳቢ ያደረገው ተኩስ አቁም ለሁለት ወራት ይዘልቃል ተብሏል
የየመን ተፋላሚ ወገኖች በጊዜያዊነት ተኩስ ለማቆም ተስማሙ፡፡
ተፋላሚ ወገኖቹ የሮመዳን የጾም ወራትን ታሳቢ በማድረግ ተኩስ ለማቆም መስማማታቸውን በየመን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ሃንስ ግሩንድበርግ አስታውቀዋል፡፡
ስምምነቱ በየመንና በድንበሮቹ የሚደረጉ የትኛውንም ዐይነት ውጊያዎች በጊዜያዊነት ለማቆም የሚያስችል ነው፡፡
ከሁለቱም አካላት ጋር በተናጠል ማውራታቸውን ያስታወቁት ልዩ መልዕክተኛው ተኩስ አቁሙ ለሁለት ወራት የሚዘልቅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ተኩስ አቁሙን ከዚያም በላይ ለማስቀጠል እንደሚቻል ተስፋ ማድረጋቸውንም ነው ግሩንድበርግ ያስታወቁት፡፡
የመናውያን በረመዳን የጾም ወር ዋዜማ የተሰማውን አዲስ ብስራት በተስፋና በስጋት ተቀብለውታል፡፡ ተኩስ መቆሙ ቢያስደስታቸውም ላይከበር ይችላል በሚል መስጋታቸው አልቀረም፡፡
7 ዓመታትን የዘለቀው የእርስበርስ ጦርነት በርካቶችን እጅግ አስከፊ ለሆኑ ችግሮችና መፈናቀሎች ሲዳርግ የ250 ሺ ገደማ የመናውያንን ህይወት ቀጥፏል፡፡
ኢትዮጵያ የሀውሲ አማጺያን ለአካባቢው ሰላም አስጊ መሆናቸውን ገለጸች
ስምምነቱን ያወደሱት የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለሰላም መንገድ ሊጠርግ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ከአሁን ቀደም የተደረጉ ተመሳሳይ ስምምነቶች ተደጋግመው በመጣሳቸው ምክንያት የታሰበውን ዘላቂ ሰላም ለማሳካት ሳይቻል መቀረቱን ጉቴሬዝ አልሸሸጉም፡፡
ተኩስ አቁሙ ሉከበርና ሊተገበር እንደሚገባ ያሳሰቡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው የእርስ በእርስ ጦርነቱ ማብቂያ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የረመዳን የጾም ወራትን ታሳቢ አድርጎ የተደረሰው ስምምነት ከጾሙ የመጀመሪያ ቀን ከዛሬ ከቅዳሜ የሚጀምር ነው፡፡ በስምምነቱ መሰረትም ነዳጅን ጨምሮ የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎች በወደብ ከተማዋ ሆዴይዳ በኩል ወደ የመን እንዲገቡና ከሆዴይዳ ወደ ሰንዓ በረራዎች እንዲኖሩ የሚኖሩ ይሆናል፡፡
የመን ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ በእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች፡፡ በ2012ቱ ምርጫ ስልጣን ይዘው የነበሩትን አብዲረቡ መንሱር ሃዲን ከሃገር እንዲሸሹ ያስገደደ ጦርነት ውስጥ የገቡት የሃውሲ አማጽያንም የተመረጠ ነው ከሚባልለት የሃገሪቱ መንግስት እና በሳዑዲ ከሚመራው የአረብ ጥምር ጦር ጋር በመዋጋት ላይ ይገኛሉ፡፡
አማጽያኑ በቅርቡ በሳዑዲ አረቢያ እንዲሁም በአረብ ኤሚሬቶች የነዳጅ ዴፖዎች እና የሲቪሊያን መገልገያ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ሰንዝረው እንደነበር ይታወሳል፡፡