በፓሪስ ኦሎምፒክ በርካታ ሜዳልያዎችን እንደሚያገኙ ግምት ያገኙ ሀገራት እነማን ናቸው?
ከ206 ሀገራት የተውጣጡ ከ10 ሺህ በላይ አትሌቶች በተለያዩ የውድድር አይነቶች ይሳተፋሉ
እስካሁን ከ8.6 ሚሊየን በላይ የስታድየም መግቢያ ትኬቶች ተሸጠዋል
በመጪው አርብ በፈረንሳይ ፓሪስ በሚጀመረው የ2024 ኦሎምፒክ ውድድር የሜዳልያ ሰንጠረዥ ቅድመ ግምት የተሰጣቸው ሀገራት ዝርዝር ይፋ ተደርጓል፡፡
በበጋ እና የክረምት ኦሎምፒክ ውድድሮች በበርካታ የውድድር አይነቶች 592 አትሌቶችን የምታሳትፈው አሜሪካ በሜዳልያ ሰንጠረዡ ቀዳሚ ደረጃ እንደምትይዝ ትጠበቃለች።
ሀገሪቱ በውድድሩ 37 ወርቅ 34 ብር እና 52 የነሀስ በአጠቃላይ 123 ሜዳልያዎችን ልታሸንፍ እንደምትችል ነው የተገመተው።
አሜሪካ በቅድመ ግምቱ እንደተመላከተው በዘንድሮው አመት በሜዳልያ ሰንጠረዡ የቀዳሚነቱን ስፍራ የምታገኝ ከሆነ ለተከታታይ 8 ዙሮች የውድድሩን በርካታ ሜዳልያ በመወሰድ ታሪክ የምታስመዘግብ ሲሆን፤
በተጨማሪም በ2021ዱ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ከነበራት የሜዳልያ ብዛት ተጨማሪ አስር ሜዳልያዎችን የምታገኝ ይሆናል፡፡
በአለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ስታትስቲካል ትንታኔዎችን የሚያወጣውን ኔልሰን ግራስኖት ጠቅሶ ዩሮ ኒውስ እንደዘገበው ከአሜሪካ በመከተል ቻይና በውድድሩ ብዙ ሜዳሊያ ከሚያገኙ ሀገራት መካከል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
በኮቪድ ምክንያት ተራዝሞ በነበረው የ2021ዱ ኦሎምፒክ አሜሪካ እና ቻይና የአንደኛ እና ሁለተኛነት ደረጃውን ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል፡፡
በዘንድሮው ኦሎምፒክ በርካታ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ የአሜሪካ ቀንደኛ ተቀናቃኝ ልትሆን እንደምትችል የምትጠበቀው ቤጂንግ 36 ወርቅ 29 ብር እና 22 የነሀስ በአጠቃላይ 87 ሜዳልያዎችን ልታሸንፍ እንደምተችል የተገመተ ሲሆን በወርቅ ሜዳልያ ብዛት አሜሪካ ልትበልጥ የምትችልበት እድል ስለመኖሩም ተሰምቷል፡፡
አሜሪካ እና ቻይናን በመከተል ብሪታንያ በ62 ፈረንሳይ በ56 ሜዳልያ በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት መካከል በተርታ ተቀምጠዋል፡፡
ከመክፈቻው እለት ጀምሮ ለ17 ቀናት የተለያዩ ውድድሮችን የምታስታናግደው ፈረንሳይ እስካሁን ባለው ከ8.6 ሚሊየን በላይ የስታድየም ትኬቶችን ሽጣለች፡፡ ይህም በ1996 በአትላንታ ኦሎምፒክ ተይዞ የነበረውን የትኬት ሽያጭ ክብረወሰን ያሻሻለ መሆኑ ታውቋል፡፡
33ኛው የኦሎምፒክ ውድድር በ35 ቦታዎች ላይ ሲካሄድ አብዘሀኛው ውድድር በፈረንሳይ ዋና ከተማ ይደረጋል፤ ሊል ፣ ማርሴል፣ ሊዮን እና ኒስ በተጨማሪ ውድድሮች የሚካሄዱባቸው ከተሞች ናቸው፡፡
ከ206 ሀገራት የተውጣጡ ከ10 ሺህ 500 በላይ አትሌቶች በሚሳተፉበት ውድድር አሜሪካ በ592 አትሌቶች በመወከል ቀዳሚዋ ስትሆን ፈረንሳይ 573 ፤ አውስትራሊያ 460፣ ጀርመን 427 አትሌቶችን በማሳተፍ ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡