ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ የምትጠብቅበት ውድድር
የ5 ሺህ ሜትር ሴቶች ፍጻሜ ምሽት 4 ስአት ከ15 በስታድ ደ ፍራንስ ይደረጋል
በፓሪስ ኦሎምፒክ የሜዳልያ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ በአንድ የብር ሜዳልያ 52ኛ ደረጃን ይዛለች
10ኛ ቀኑን በያዘው የፓሪስ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ምሽት ይደረጋሉ።
ምሽት 4 ስአት ከ15 ላይ በስታድ ደ ፍራንስ የሚካሄደው የሴቶች 5000 ሜትር የፍጻሜ ውድድርም ኢትዮጵያ በፓሪስ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ እንደምታገኝ የሚጠበቅበት ነው።
በውድድሩ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ፣ እጅጋየሁ ታዬ እና መዲና ኢሳ ይሳተፋሉ።
በማጣሪያው ቀዳሚ ሆና ያጠናቀቀችውና ከሶስት ሳምንት በፊት የራሷን የ1 ሺህ 500 ሜትር ክብረወሰን የሰበረችው ኬንያዊቷ አትሌት ፌይዝ ኪፕየገን ኢትዮጵያውያኑን አትሌት ትፈትናለች ተብሎ ይጠበቃል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ኔዘርላንዳዊ ሲፋን ሀሰንም በፓሪስ የወርቅ ሜዳልያ ለማጥለቅ ከሚፎካከሩት መካከል ተጠቃሽ ናት።
ከአራት አመት በፊት በቶኪዮ በተካሄደውና ሲፋን ባሸነፈችበት የ5000 ሜትር ውድድር አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ ሶስተኛ ሆና ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።
አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ በአሜሪካ ዩጂን ባለፈው አመት የ5 ሺህ ሜትር ውድድር ክብረወሰንን (14፡00.21) በእጇ ማስገባቷ ይታወሳል።
ዛሬ ምሽት 4 ስአት ከ47 ላይ ደግሞ የ800 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል።
በውድድሩ ኢትዮጵያ በማጣሪያው ተስፋ ባሳዩት አትሌት ፅጌ ዱጉማ እና ወርቅነሽ መለሰ ትወከላለች።
128 አመት እድሜ ባለው ግዙፍ የስፖርት መድረክ 58 ሜዳያዎችን ያገኘችው ኢትዮጵያ በፓሪስ እስካሁን በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ውድድር የብር ሜዳልያ ብቻ ነው ያገኘችው።
በ33ኛው ኦሎምፒክ የደረጃ ሰንጠረዥም 52ኛ ላይ ተቀምጣለች።