አንዳንድ ሀገራት ለአትሌቶቻቸው ተጨማሪ ምግብ በራሳቸው ወጪ እያቀረቡ መሆኑ ተሰምቷል
የኦሎምፒክ አትሌቶች በትራንስፖርት እና የምግብ አቅርቦት ላይ ቅሬታ ማቅረባቸው ተነገረ፡፡
አትሌቶቹ የምግብ ጥራት እና መጠን ላይ ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን በተለይ የስጋ እና የእንስሳት ተወጽዖ ምግቦች እጥረት በመኖሩ መቸገራቸውን ነው የገለጹት፡፡
የፓሪስ ኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ በዛሬው እለት ከአትሌቶቹ ጋር ባደረገው ስብሰባ በፈረንሳይ የሚመረቱ የስጋ እና የእንስሳት ተዋጽኦ የምግብ አይነቶች አቅርቦትን እንደሚጨምር ቃል ገብቷል፡፡
ኬር ፎር የተሰኘው የምግብ ማቅረብ አገልግሎት የሚሰጥ ፈረንሳዊ ተቋም ለ15000 አትሌቶች በቀን 40 ሺህ ምግብ ለማቅረብ ከአዘጋጆቹ ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል።
የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤቲየን ቶቦይስ መሰል ቅሬታዎች በርካታ ሰዎች በሚታደሙባቸው ሁነቶች ላይ ያጋጥማል፤ አትሌቶች ያቀረቡትን ቅሬታ ለመቅረፍ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 700 ኪሎግራም እንቁላል እና አንድ ቶን የስጋ ምርት አትሌቶቹ ወደሚገኙበት መንደር እየተጓጓዘ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
በምግብ እጥረት እና ጥራት ላይ አትሌቶቹ ያነሱትን ቅሬታ ተከትሎ 6 የኮርያ የዋና ተወዳዳሪዎች ከሚወዳደሩበት ስፍራ አቅራቢያ ወደሚገኝ ሆቴል ውስጥ እንዲዘዋወሩ የኮርያ ኦሎምፒክ ፌደሬሽን ፈቃድ ሰጥቷል፡፡
460 አትሌቶች ያሉት የአውስትራሊያ ልዑክ በበኩሉ 3 ቶን ቱና አሳ እና ሌሎችንም ምግቦች ቀደም ብሎ አዘጋጅቶ በመምጣቱ የምግብ እጥረት ችግሩን እንደተቋቋመ አስታውቋል፡፡
ከዚህ ባለፈም አትሌቶቹ ማቀዝቀዣ በሌላቸው አውቶብሶች ውስጥ ለረጅም ሰአት ወደ ውድድር ስፍራው የምናደረገው ጉዞ አድካሚ ሆኖብናል በሚል ቅሬታ አቅርበዋል፡፡
የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤቲየን ቶቦይስ ተጨማሪ ዘመናዊ አውቶብሶችን ለአትሌቶቹ ማጓጓዣነት ለማሰማራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ከምግብ ጥራት እና መጠን ጋር የተነሳው ቅሬታ ግን ከዛሬ ጀምሮ እንደሚቀረፍ ተናግረዋል፡፡