ኢትዮጵያ በፓሪስ ፓራሊምፒክ 2ኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች
አትሌት ያየሽ ጌቴ በ1500 ሜትር በዐይነ ሥውራን የሩጫ ውድድርን ክብረወሰን በመስበር አሸንፋለች
አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ በፓራሊምፒክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ማስገኘቷ ይታወቃል
አትሌት ያየሽ ጌቴ በ2024ቱ የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ለኢትዮጵያ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ አስገኝታለች።
አትሌት ያየሽ ጌቴ ከአሯሯጯ ክንዱ ሲሳይ ጋር በመሆን በ1500 ሜትር በዐይነ ሥውራን ሙሉ በሙሉ ምድብ 1ኛ ደረጃን በመያዝ በማጠናቀቅ ነው ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው።
ውድድሩን 4:27:68 በሆነ ሰዓት የገባችው አትሌት ያየሽ በራሷ የተያዘውን የዓለም ክብረ ወሠን በመስበር ጭምር ነው ውድድሩን ያጠናቀቀችው።
ያየሽ ከዚህ ቀደም የዓለም ክብረ ወሰንን ይዛ የነበረው በጃፓን ኮቤ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በተካሄደው 11ኛው የዓለም የፓራአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ እንደነበር ይታወሳል።
በወቅቱ የገባችበት ሰዓት 4 ደቂቃ ከ31 ሴኮንድ ከ77 ማይክሮ ሴኮንድ ነበር።
ለ17ኛ ጊዜ በፈረንሳይ ፓሪስ እየተካሄደ በሚገኘው የፓራሊምፒክ ውድድር ላይ አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ በ2024 የፓሪስ የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ ማስገኘቷ ይታወቃል።
አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ያስገኘችው ሜዳልያ በ 1,500 ሜትር ጭላንጭል ውድድር መሆኑ ይታወቃል።
አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ በፓራሊምፒክ ውድድር ታሪክ ለኢትዮጵያ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ያመጣች ሲሆን ከሶስት ዓመታት በፊት በቶኪዮ ፓራሊምፒክ ውድድር ለኢትዮጵያ በታሪክ የመጀመሪያ የፓራሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘት ችላለች።
ኢትዮጵያ በፓሪስ በፓራሊምፒክ ውድድር ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ምገኘቷን ተከትሎ በሜዳያ ሰንጠረዡ 26ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች።
በ2024 የፓሪስ ፓራሊምፒክ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ እስካሁን 35 ወርቆችን የሰበሰበችው ቻይና፤ በአጠቃላይ በ75 ሜዳሊያዎች 1ኛ ደረጃ ለይ ትገኛለች።
ብሪታኒያ 23 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ጨምሮ በድምሩ በ43 ሜዳሊያዎች 2ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፤ አሜሪካ በ8 የወርቅ ሜዳሊያ በድምሩ በ29 ሜዳሊዎች 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።