የፒተርስበርግ የአየር ንብረት ለውጥ ምክክር በበርሊን ተጀምሯል
በምክክሩ አረብ ኤምሬትስ በምታስተናግደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ አጀንዳዎች ይለያሉ
በበርሊን ትናንት በተጀመረው ጉባኤ ከ40 በላይ ሀገራት ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ
አረብ ኤምሬትስ እና ጀርመን በጋራ ያዘጋጁት የ“ፒተርስበርግ የአየር ንብረት ለውጥ ምክክር” ትናንት በበርሊን ተጀምሯል።
በምክክሩ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጀበርን ጨምሮ የ40 ሀገራት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።
በምክክሩ በአረብ ኤምሬትስ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ(ኮፕ28) ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ አጀንዳዎች እንደሚለዩ ይጠበቃል።
በጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ዛሬም ቀጥሎ እየተካሄደ ባለው ምክክር ጀርመንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ሆነው ለተመረጡት ዶክተር ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጀበር ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሊና ቤርቦክ “ዶክተር ሱልጣኝ አልጀበር ለያዙት አለምን ከበካይ ጋዝ ልቀት ነጻ የማድረግ ትልም ማንኛውንም ድጋፍ እናደርጋለን” ብለዋል።
በህዳር ወር 2023 የሚደረገው የኮፕ28 ጉባኤም የአለምን ሙቀት ለመቀነስ የሚያስችል ስምምነት ይደረስበታል ብለው እንደሚያምኑም ነው የተናገሩት።
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ክፉኛ እየተጎዱ የሚገኙ ሀገራትን ለመደገፍና የገጠማቸውን ጉዳት ለማካካስም ከፍተኛ ብክለት የሚያደርሱ ሀገራት ቁርጠኛ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ጀርመን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሚውሉ ስራዎች 6 ቢሊየን ዩሮ ብትመድብም የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ብዙ የሚቀራት ነገር እንዳለም አልሸሸጉም።
የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር በበኩላቸው፥ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ የተደረሱ ስምምነቶችን ገቢራዊ በማድረግ ተምሳሌት ለመሆን እየሰራች መሆኑን አንስተዋል።
ሀገራት በተለይ የሃይል ምንጫቸውን ከብክለት የጸዳ እንዲያደርጉና በብክለት ለሚመጣ ጉዳት ሊደረግ ስለሚገባው ካሳ በጥልቀት መክረው ውሳኔ ላይ መድረስ እንዳለባቸውም ነው ያሳሰቡት።
የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር (የኮፕ27 ፕሬዝዳንት የነብሩ) ሳሜህ ሹክሪም በሻርም አልሼክ በተደረገው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት በትብብር እንዲሰሩ መግባባት ላይ መደረሱን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ በጉባኤው ቃል የተገቡ ጉዳዮች አፈጻጸም ብዙ እንደሚቀረው ነው በጀርመን በሚገኙት የግብጽ አምባሳደር በኩል ባስተላለፉት መልዕክት የተናገሩት።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው፥ ሀገራት ከጂኦፖለቲካዊ ቅራኔ በመውጣት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የአለም የሙቀት መጠን በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ ከጨመረ እጅግ አደገኛ ነው ያሉት ጉቴሬዝ፥ ሀገራት የሃይል አማራጫቸውን ከብክለት የጸዳ ለማድረግ የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙት አሳስበዋል።
ከ2010 ጀምሮ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች ከመደረጋቸው በፊት የሚካሄደው የፒተርስበርግ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ምክክር በየአመቱ መካሄዱን ቀጥሏል።
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝም በዛሬው እለት በዚሁ ምክክር ላይ መልዕክታቸውን እንደሚያስተላልፉ ይጠበቃል።