ፊሊፒንስ የጦር ሄሊኮፕተሮችን ከሩሲያ ለመግዛት የፈጸመችውን ስምምነት እንደማትሰርዝ አስታወቀች
ዱቴርቴ በአንድ ወቅት ‘ሮልሞዴሌ’ ነው በሚል የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ያደንቁ ነበር
የጦር ሄሊኮፕተሮቹ ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት በፊት የታዘዙ ናቸው
የጦር ሄሊኮፕተሮችን ከሩሲያ ለመግዛት የፈጸመችውን ስምምነት እንደማትሰርዝ ፊሊፒንስ አስታወቀች
የፊሊፒንስ ጦር ከሩሲያ የጦር መሳሪያዎች መግዛቱን እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡
ጦሩ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ ቀደም ብሎ ያዘዛቸውን 17 ሄሊኮፕተሮች ግዢ በስምምነቱ መሰረት እንደሚቀበልም አስታውቋል፡፡
ደቡብ እስያዊቷ ፊሊፒንስ 17 ሚግ የጦር ሄሊኮፕተሮችን ከሩሲያ ለመግዛት የ12 ነጥብ 7 ቢሊዮን ፔሶ (243 የአሜሪካን ዶላር) ስምምነት አድርጋ ነበር፡፡
ስምምነቱ የጦር ሄሊኮፕተሮቹን በ2 ዓመታት ውስጥ አምርቶ ለማስረከብ የሚያስችል ነው፡፡
የጦሩ አዛዥ ዴልፊን ሎሬንዛና ሄሊኮፕተሮቹን በስምምነቱ መሰረት የማድረስ ግዴታ የሩሲያ ነው ሲሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ያስታወቁት፡፡
ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚውሉት ሄሊኮፕተሮቹ ግዥ ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት በፊት የታዘዘ ነው፡፡
ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን ወረራ በአስቸኳይ ታቁም ወታደሮቿንም ታስወጣ በሚል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ከደገፉ ሃገራት መካከል አንዷ ፊሊፒንስ ነች፡፡
ፕሬዝዳንት ዱቴርቴም ቢሆኑ በወረራው ስጋት እንደገባቸው መግለጻቸው ተነግሯል ምንም እንኳን በይፋ ሲያወግዙ ባይደመጡም፡፡
ይህን ተከትሎ ሩሲያ ስምምነቱን ትሰርዝ ወይ ታዘገይ እንደሆነ የተጠየቁት ሎሬንዛና እንዲህ ዐይነት እድል ይኖራል ብለን አንጠብቅም ብለዋል፡፡
ዱቴርቴ በአንድ ወቅት ‘ሮልሞዴሌ’ ነው በሚል የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ያደንቁ ነበር፡፡