በማስነጠስ ምክንያት ጉዳት ያጋጠው የቦልተኑ ተጨዋች ቪክተር አዴቦይጆ ነው
"ከባድ ማስነጠስ" ልምድ ያለውን ተጨዋች "ለከባድ የጀርባ ጉዳት" ዳርጓል።
እንደስካይ ኒውስ ዘገባ ከሆነ የቦልተን ዋንደረርስ ተከላካይ ተጨዋች የሆነው ቪክተር አዴቦይጆ በቀጣይ ማክሰኞ 'በብሪስቶል ስትሪት ሞተርስ ትሮፊ ግሩፕ' ጨዋታ ላይ ለመሳተፍ እቅድ ይዞ ነበር።ነገርግን በጀርባ እና በጎድኑ ላይ ምቾት በማጣቱ ምክንያት ከቡድኑ ውጭ ለመሆን ተገዷል።
በጉዳት እና በአለምአቀፍ ረፍት ምክንያት የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጨዋቾቻቸውን ያጡት አሰልጣኝ ኢያን ኢቫት ጉዳቱ "በከባድ ማስነጠስ" ምክንያት የተከሰተ ነው ብለዋል።
"አመናችሁም አለማነችሁ፣ የቪክተር ከባድ የጀርባ ህመም የተቀሰቀሰው በማስነጠስ ነው" ሲሉ አሰልጣኙ ተናግረዋል። ከእዚያ ጊዜ ጀምሮ የ26 አመቱ አዴቦይጆ በህክምና ላይ ነው።
"በጎድኖቹ መካከል የመሰንጠቅ ስሜት ተሰምቶታል። የስካን ውጤቱን እስከምናየው ድረስ የጡንቻ ጉዳይ ይሆናል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር" ብሏል ኢቫት።
አሰልጣኙ አክሎ እንደገለጸው ችግሩ የተከሰተው ከቻርልተን ጋር በተደረገው ጨዋታ ወቅት ነው። "በጊዜው ደህና ነበር፤ ነገርግን ቆይቶ ክፉኛ አስነጠሰው። ቪክተር ኃይለኛ ልጅ ነው፣ ማስነጠሱም እንደዚያው ነው።"
በመጀመሪያው የውድድር ዘመን አራት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን የሰበሰበው ቦልተን በሊግ ዋን 18ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ከባሮው ጋር የነበራቸውን ጨዋታ 3-2 ማሸነፍ ችለዋል።