የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ የሚያሠጋ ነገር ካጋጠመ ሰራዊቱ በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ወደ ትግራይ ክልል ይገባል- ጠ/ሚ ዐቢይ
በዚህ ወቅት ወደ ትግራይ ክልል መግባት ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው እንደሚያመዝንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል
“መከላከያ በያዛቸው አካባቢዎች ላይ እንዲቆይ የወሰንነው የሚያስገኘውን ዘላቂ ጥቅም ከግምት አስገብተን ነው” ብለዋል-
በዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት የተጀመረው ማጥቃት ህወሐት ከአማራና ከአፋር ክልሎች በማስወጣት የመጀመሪያውን ግብ ማሳካቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማምሻውን ባወጡት መግለጫ፤ “መንግስት የመከላከያ ሠራዊቱ አሁን በያዛቸው አካባቢዎች ላይ እንዲቆይ ትእዛዝ ሰጥቷል፤ ይሄንን ውሳኔ የወሰንነው በስሜት ሳይሆን የሚያስገኘውን ዘላቂ ጥቅም ከግምት አስገብተን ነው” ብለዋል።
- “ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ”- ጠ/ሚ ዐቢይ
- ለህወሓት የተሰለፉ ሁሉ እጃቸውን እንዲሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥሪ አቀረቡ
“ኢትዮጵያን በዘላቂነት ባለድል የማያደርግ አካሄድ ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለጠላቶቻችን ብርታትን የሚፈጥር፣ የሽብር ቡድኖች እድሜያቸውን የሚያረዝሙበትን ሰበብ እንዲያገኙ መፍቀድ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አለፍ ሲልም በስሜት የሚወሰኑ ወታደራዊ ውሳኔዎች ሀገራችንን በተራዘመ ጦርነት አዙሪት ውስጥ እንድትዘፈቅ ያደርጋል” ብለዋል።
“ኢትዮጵያን ለማዳከም የተከፈተው ዘመቻ መልከ ብዙ ነው” ያሉ ሲሆን፤ ይህም ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የመረጃ ጦርነቶች በሀገሪቱ ላይ እየተካሄዱ መሆኑን እና ይህም በተቀናጀና በረቀቀ መልኩ እየተፈፀመ እንደሆነም አስረድተዋል።
መንግሥት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ህልውና ላይ የተከፈተውን ግልጽና ረቂቅ ዘመቻ ለመመከትና ለመቀልበስ ብሎም በዘላቂነት የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለማረጋገጥ የነደፈው ዕቅድ ሁለገብና ሁሉንም ግንባሮች ለመመከት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።
መንግሥት የሚወስናቸው ውሳኔዎች ሁሉንም ግንባሮች መሠረት ያደረጉ እንጂ በተናጠል እይታ የታጠሩ አይደሉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የመጀመሪያው እቅድ ህወሓትን ከአፋርና ከአማራ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ማጽዳት ነው፤ ይሄንንም መቶ በመቶ ሊባል በሚችል መልኩተሳክቷ ብለዋል።
“ሠራዊታችንንም ስትራቴጂያዊ በሆኑ ቦታዎች እንዲሠፍር በማድረግ የጠላትን እንቅስቃሴ በአንክሮ እንዲከታተል አድርገናል፤ ይሄንን እንድንወስን ያደረጉን ብዙ ምክንያቶች አሉ” ሲሉም አስረድተዋል።
ከእነዚህም አንደኛው “የግዛት አንድነታችንና ሉዓላዊነታችነን የሚያሠጋ ነገር ከገጠመን በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ወደ ትግራይ ክልል ገብቶ የሀገርን ደኅንነት ለማስከበር የመከላከያ ሠራዊቱ ሕገ መንግሥታዊ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም አለበት” ብለዋል።
በሌላም በኩል “ሕወሐትና አፈ ቀላጤዎቹ መንግሥትንና ሠራዊቱን ለመክሰስ ወደ አዘጋጁት የሤራ ወጥመድ መግባት እንደሌለብን እናምናለን፤ በዚህ ወቅት የእኛ ወደ ክልሉ መግባት ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው” ሲሉም አስታውቀዋል።
የትግራይ እናቶች ይሄንን ሁሉ ምስቅልቅል ያመጣባቸውንና ልጆቻቸውን ነጥቆ ያስጨረሰባቸውን “አሸባሪ ኃይል” መጠየቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
“ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄንን አሸባሪ ከጫንቃው ላይ ያስወገደው በመራራ ትግሉ ነው፤ የትግራይ ሕዝብም እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ይሄንን አሸባሪ ታግሎ የማስወገድ አቅምና ችሎታው አለው” ብለዋል።
ድጋፍና እርዳታ በአስፈለገ ጊዜም የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከክልሉ ሕዝብ ጎን ይቆማል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የማንኛውም ውሳኔያችን መርሕ ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ድል እንድትጎናጸፍ ማስቻል ነው፤ ግዛታዊ አንድነታችን የሚጠበቅበትና በዘላቂነት ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆንበትን መንገድ መቀየስ ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።
“እንደ ከዚህ በፊቱ አንድነታችን ጠብቀን እስከቆምን ድረስ መቼም ቢሆን ኢትዮጵያ አትሸነፍም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የኢትዮጵያ ድል መሠረቱ የጠላት ድክመት ሳይሆን የእኛ ብርታትና ትብብር መሆኑን አውቀን፣ ይበልጥ አንድነታችንን አጠንክረን መቆም ይገባናል” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።