ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ኃይለማርያም ደሳለኝ አዲስ ሹመት አገኙ
ሁለቱ ኢትዮጵያዊን ፖለቲከኞች አፍሪካዊ ተቋማትን እንዲመሩ መመረጣቸው ተገልጿል
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢጋድ የቱሪዝም ሻምፒዮን ሲሆኑ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ ትሬድማርክ አፍሪካ የተሰኘው አህጉራዊ ተቋም የቦርድ ሊቀመንበር ሆነዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ኃይለማርያም ደሳለኝ አዲስ ሹመት አገኙ፡፡
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ወይም ኢጋድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የቱሪዝም ሻምፒዮን አድርጎ መምረጡን አስታውቋል፡፡
ለሶስት ዓመታት ይቆያል የተባለው ይህ ሀላፊነት በምስራቅ አፍሪካ ቱሪዝም እና ባህል እንዲስፋፋ ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር እና አካባቢ ጥበቃ ስራዎች እና መሰል ትብብሮች እንዲጎለብቱ ከየሀገራቱ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩም ተገልጿል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዋና መቀመጫውን ኪጋሊ ሩዋንዳ ያደረገው ትሬድማርክ አፍሪካ የተሰኘው አህጉራዊ ተቋምን በቦርድ ሊቀመንበርነት እንዲመሩ መርጧቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በነዳጅ ተሽከርካሪዎች ላይ የጣለችውን እገዳ ታነሳ ይሆን?
ድርጅቱ እንዳስታወቀው ላለፉት ስምንት ዓመታት የድርጅቱ ቦርድ ሊቀመንበር የነበሩት የቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ምክትል ኮሚሽነር ኬንያዊው ኢራስመስ ሙዌቻ በኢትዮጵያዊው ኃይለማርያም ደሳለኝ ተተክተዋል፡፡
ትሬድማርክ አፍሪካ በንግድ እና ስራ ፈጠራ የተሰማሩ አፍሪካዊያን ወጣቶችን በመደገፍ የሚታወቅ ተቋም ሲሆን ኃይለማርያም ደሳለኝ አፍሪካዊን ነጋዴዎችን ከመደገፍ ባለፈ በዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓት ውስጥ የአፍሪካ ሚና እንዲጎለብት ማድረግ ዋነኛ ተልዕኳቸው ሆናል ተብሏል፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አፍሪካዊ ተቋማትን ሲመሩ የአሁኑ የመጀመሪያቸው ሳይሆን ከዚህ በፊት የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ወይም አግራ የቦርድ አመራር ሆነውም አገልግለዋል፡፡