ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጅቡቲ የገቡት በፕሬዝዳንት እስማኤል በዓለ ሲመት ላይ ለመገኘት ነው
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጅቡቲ መግባታቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል፡፡
ጽ/ቤቱ እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልዑካናቸው ወደ ስፍራው ያቀኑት በቅርቡ በጅቡቲ በተካሄደው ምርጫ አሸናፊ በሆኑት በፕሬዝዳንት እስማኤል ኡመር ጉሌህ በዓለ ሲመት ላይ ለመገኘት እና ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ነው፡፡
የጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጉሌህ በሀገሪቱ የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለ5ኛ ጊዜ ማሸነፋቸው ተከትሎ በዓለ ሲመታቸው ይከናወናል፡፡
ጉሌህ በሀገሪቱ በተካሄደው ምርጫ ከተሰጠው 177 ሺህ 391 ድምፅ ውስጥ 98 በመቶ በማግኘት ማሸነፋቸው መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡
ፕሬዘዳንቱ ላለፉት 22 ዓመታት በስልጣን ላይ መቀጠላቸው ሳያንስ ለተጨማሪ ዓመታት ጅቡቲን ለመምራት በምርጫው መወዳደራቸውን ፓርቲዎች በወቅቱ ተቃውመው ነበረ።
ከአንድ ፓርቲ በስተቀር ሌሎቹ ፓርቲዎች ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸው ይታወሳል፡፡
የቀድሞው ወታደር እና አሁን በንግድ ስራ የሚተዳደሩት ዘከሪያ እስማኤል ፋራህ ብቸኛው በጅቡቲ ምርጫው የተሳተፉ ተቃዋሚ ፓርቲ ነበሩ።
አንድ ሚሊየን የማይሞላ ሕዝብ ብዛት ያላት ጅቡቲ ከጠቅላላ ህዝቧ 14 በመቶዎቹ ስር በሰደደ ድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ የዓለም ባንክ መረጃ ያስረዳል።
ሀገሪቱ ካላት አቀማመጥ አንጻር የዓለም ኃያላን ሀገራት ወታደራዊ ማዘዣዎቻቸውን ገንብተውባታል፡፡ ጅቡቲ ከ95 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ዕቃዎች የሚተላለፉት በጅቡቲ ወደብ ነው፡፡