ጠ/ሚንስትር ዐቢይ አዲስ አበባን የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የውስጥና የውጭ ኃይሎች እየሞከሩ ነው አሉ
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በከፍተኛ ቁርኝነት መስራት አለባቸው ብለዋል

ጠቅላይ ሚንስትሩ “ሀገሪቱ ከ ወራት በፊት ከነበረችበት አሁን ላይ ሰላሟ እየተሻሻለ ነው” ብለዋል
የመንግስታቸውን የመንፈቅ አፈጻጸም በሚመለከት ከህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ፤ የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት በስፋት ተጠይዋል።
ሀገሪቱ ከወራት በፊት ከነበረችበት ሰላሟ እየተሻሻለ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ የሰሜኑ ጦርነት መቋጨት አንድ እርምጃ ነው ብለዋል።
ሙሉዕ ሰላም ለማስፈረም በመንግስታቸው የተጀመሩ ስራዎች እንዳሉም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባን የጸጥታ ጉዳይ በሚመለከት የከተማዋን ፍልሰት በቀዳሚነት ያነሱ ሲሆን፤ በቅርቡ ተጠና ባሉት ጥናት ባለፉት ሁለት ዓመታት ፍልሰት በእጅጉ መጨመሩን ተናግረዋል።
- "የኢትዮጵያ አርሶአደር ከተሜው እንዲራብ መፍቀድ የለበትም” -ጠ/ሚ አብይ
- "በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ነገር ይቋጫል፤ ኢትዮጵያ ሰላም ትሆናለች"- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
በህገ-ወጥ መንገድ ከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ 96 በመቶ የሚሆኑ ሰዎቸ የአዲስ አበባ ነዋሪ አይደሉም ብለዋል።
ይህን በሚመለከት ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ "ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ፍልሰት የመንግስት ስልጣን በኃይል ለመቆጣጠር ነው" ማለታቸው ይታወሳል።
ይህን ሀሳብ በመደገፍ የተናገሩ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፤ ከተማዋን የግጭት ማዕከል ለማድረግ የሚሰሩ ኃይሎች አሉ ብለዋል።
"አዲስ አበባን የብጥብጥ ማዕከል ማድረግ አለብን የሚሉ የውጭና የሀገር ውስጥ ኃይሎች አሉ። በአንድ ቀበሌ ፊርማ መታወቂያ የያዙ አንድ ባስ ሙሉ እናገኛለን። ተሰባስበው አንድ ቦታ እናገኛቸዋለን። ከወለጋም ይምጣ ከጎጃም። ሰኔና ሰኞ የተገናኘ ሲመስላቸው፣ በህዝብ በዓላት አበል ተከፍሏቸው ይመጣሉ። መሳሪያ፣ ገንዘብ ፣ፈንጅ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንይዛለን። የተጠናከረ ስራ መስራት እንቀጥላለን" ብለዋል።
ቁጥጥሩ እንደሚጠናከር የገለጹም ሲሆን፤ እንግልትን ለመቀነስም የጸጥታ ኃይሎች ይሰራሉ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከጸጥታ አካል ጋር በከፍተኛ ቁርኝነት መስራት አለባችሁ ሲሉም ጠቅላይ ሚንስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።