ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰቆጣ የህብረተሰብ ተወካዮችን እያወያዩ ነው
የደህንነት ሹሙን ጨምሮ ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙም በውይይት መድረኩ ተገኝተዋል
በውይይቱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ተገኝተዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮችን እያወያዩ ነው፡፡
ውይይቱ በሰቆጣ ከተማ ነው በመካሄድ ላይ ያለው፡፡
እንደ አሚኮ ዘገባ በውይይቱ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ተገኝተዋል፡፡
ሌሎች ከፍተኛ የዞኑና የክልሉ እንዲሁም የፌዴራል ባለስልጣናትም ተገኝተዋል።
ውይይቱ በዋናነት የብሔረሰብ አሥተዳደር ዞኑ የሚገኝበትን ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ አድርጎ የሚካሄድ ነው የተባለ ሲሆን ከተሳታፊዎች በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
ጥቂት የማይባሉ የብሔረሰብ አስተዳደር ዞኑ አካባቢዎች አሁንም በአሸባሪነት በተፈረጀው ህወሓት እጅ ናቸው፡፡
የዞኑ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች መምሪያ ሀላፊ ኮረኔል ጌታወይ ዘገዬ አሁንም ከወራሪው ነፃ ያልወጡ ወረዳዎች እና የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውንም ከሰሞኑ ከጸጥታ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በዞኑ በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ተናግረዋል፡፡
አሁንም በህወሓት እጅ ካሉ የብሔረሰብ ዞኑ ወረዳዎች መካከል አበርገሌ፣ ፃግብጅ፣ ዛታ፣ ዝቋላ እና ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳዎች በከፊል ይገኙበታል፡፡ ከነዚሁ አካባቢዎች የሚፈናቀሉና ቀያቸውን ለቀው የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር በቀን በአማካይ እስከ 2 ሺ ይደርስ እንደነበር አል ዐይን ከወር በፊት መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ጦርነቱን ተከትሎ በርካታ የአካባቢው ማህበረሰብ ከቤት ንብረቱ ከመፈናቀልም በላይ ለምግብ እጦት ተዳርጓል፡፡
የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶችም ወድመዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የተለያዩ ድጋፎች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡
እነዚህንና ሌሎች በአካባቢው ያሉ አንገብጋቢ ጉዳዮች የተመለከቱ ጥያቀዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተገኙበት በመካሄድ ላይ ባለው ውይይት ሊነሱ እንደሚችሉም ይጠበቃል፡፡