“የወደብ ጉዳይ ጊዜ ሳይሰጠው አሁኑኑ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል” ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ
ጠ/ሚ ዐቢይ ከወደብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት ሀገራት አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎትም እንደሌላት አስታወቁ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ወደብ የማግኘት መብት ላይ በህግና በቢዝነስ ማእቀፍ እንወያይ ነው ያልነው” ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “የወደብ ጉዳይ ጊዜ ሳይሰጠው አሁኑኑ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል” ሲሉ አሳሰቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም ከወደብ ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ የዛሬ 30 ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ ሁለት ወደብ ባለቤት ነበረች፤ ከ30 ዓመታት በኋላ ሁለት ወደብ በንግድ ህግ መጠቀም ወደምትችልበት ዝቅ አለች። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ጦርነት ሲቀሰቀስ የንግዱም ወደ አንድ ወደብ ዝቅ ማለቱንም አስታውቀዋል።
ባለፉት 20 ዓመታት የኢትዮጵያ የወጪ ገቢ ንግድ በ20 እጥፍ አድጓል፤ የህዝብ ቁጥርና ኢኮኖሚም በዚያው ልክአ ያደገ ነው፤ በዚህ እንዳለ በአንድ ወደብ ብቻ መጠቀም የጊዜ ጉዳይ ው እንጂ ችግር ማምጣቱ አይቀርም ብለዋል።
- ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ለመጠቀም እንደምትደራደር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገሩ
- ከአንታርክቲካ ድረስ እየመጡ ባለበት ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን መፈለጓ እንደ ስህተት መቆጠር የለበትም- የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር
“ቀይ ባህር ያስለፍለገኛል የማይል የዓለም ክፍል የለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ምነው እኛ ስንፈልገው ነውር ሆነ?” ሲሉም ጠይቀዋል። ቀይ ባህር ለእኛ ብቸኛ መተንፈሻን ነው ሲሉም ተናረዋል።
“የወደብ ጉዳይን አዲስ ጥያቄ አድርገው የሚያነሱ አሉ”፤ “እነዚህ ወገኖች የባህር ኃይል ስንገነባ የት ነበሩ፤ እኛ የባህር ኃይል ስንገነባ ለሌላ አጀንዳ ይደለም ባህር እንፈልጋለን ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
የኤርትራን እና የጎረቤት አገራትን ሉዓላዊነት ለመጉዳት የተነሳ አስመስለው የሚያቀርቡ አሉ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ የማንንም ሀገር ሉዓላዊነት የመጉዳትና የመውረር ፍላጎት የለንም ብለዋል።
አሜሪካ እና ቻይናን ጨምሮ ለዓለም ሀገራት ባስተላለፉት መልእክትም “ኢትዮጵያ ያልተገባ ጥያቄ ከህግ ውጪ አልጠየቀችም፤ ከዚህ ውጪ ጠይቃ ከሆነ እረፉ በሉን እንተዋለን፤ እኛ እንወያይ ነው ያልነው” ሲሉም ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት አገራት አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎትም የላትም፤ ነገር ግን በህግና በቢዝነስ ማእቀፍ እንወያይ ነው ያልነው፤ ምርጥ አየር መንግድ አለን እሱን እንጋራ ነው ያልነው፣ ህዳሴ ግድብን እንጋራ ነው ያልነው” ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ እያደገ ነው፤ በመሆኑም የወደብ ጉዳይ ጊዜ ሳይሰጠው አሁኑኑ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
“ረሃብ፣ ችግር ሳይመጣ ተነጋግረን ህጋዊ መፍትሄ እናብጅ ነው ያልነው፤ ጥያቄዎን ማንሳታችን እንደ ነውር ሊቆጠርም አይገባም” ብለዋል።