ሰራዊቱ ከድል በኋላ ከሚመጣ መከፋፈል ራሱን እንዲጠብቅ እና አንጃ እንዳይፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ወደ መቀሌ አቅንተው ህግ በማስከበር ዘመቻ ላይ ከሚገኙ የጦር አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሰራዊቱ የተሰጠውን ሃገራዊ እና ህጋዊ ተልዕኮ በብቃት የሚፈጽ ጠንካራ ቁመና እንዳለው በተግባር አሳይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመስግነዋል፡፡
ይህንኑ ለመግለጽ በሚል መቀሌ መገኘታቸውንም በውይይቱ ለተገኙ የጦር አመራሮች ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ ዘመናዊ የሚባል የዕዝ ማዕከል ሲቹዌሽን ሩም ገንብተን ውጊያውን በቀጥታ በአይናችን እያየን ነው የመራነው ያሉ ሲሆን ለሰጡት አመራር እና ላሳዩት ቁርጠኝነት ጄነራል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ ወደ ሰራዊቱ ተመልሰው ለድል ያበቁትን የቀድሞ ጄነራሎች አመስግነዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ለዘላለም የምታከብረው ገድል ሰርታችኋል” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
የማንም ሃገር ወታደር ቢሆን በእናንተ ልክ በእቅድ የሚያሳካ የለም ሲሉም አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
በእሳቸው ትዕዛዝ 6 ቀናቶች ቢጨመሩም ሰራዊቱ ባቀደው መሰረት ጦርነቱን በሁለት ሳምንታት ውስጥ መጨረሱን እና በጦርነቱ ከፍተኛ የማድረግ አቅም መገንባቱንም ነው የተናገሩት፡፡
“በወታደራዊ ቋንቋ ብቻም ሳይሆን በቴክኖሎጂያዊ ቋንቋ ለመነጋገር የሚችሉ ኮማንዶች ተፈጥረዋል” ነው ያሉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዡ በቴክኖሎጂ አማካይነት ጠላትን ለማፍረስ መቻሉን በመጠቆም፡፡
በመከላከያው የማድረግ አቅም ማደግ አብዛኛውን ኪሳራ ለመቀነስ እና ጦርነቱ እንዲያጥር ለማድረግ ተችሏል እንደ ጠቅላይ አዛዡ ገለጻ፡፡
ይህ ባይሆንና ልክ እንደ ህወሓት ኃይል ሁሉ ሚሳዔሎች እና ቦንቦች ተተኩሰው ቢሆን ኖሮ በመካከላችን ያለውን ጄነራል አዳምነህን ጨምሮ በጠላት እጅ ወድቀው የነበሩ 1 ሺ ገደማ ኦፊሰሮችን ለመታደግ አንችልም ነበር ሲሉም ተናግረዋል፡፡
መከላከያ ሰራዊቱ የግለሰብም ሆነ የፓርቲ ውግንና ሳይኖረው ኢትዮጵያዊ ሆኖ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡
ወንጀለኞችን በቶሎ አድኖ ለህግ እንዲያቀርብም ጠይቀዋል፡፡
“ከዚህ አንጻር ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት የሚሰማኝን የትግራይን ህዝብ ጨምሮ ሁሉም ዜጋ የተበተኑትን ወንጀለኞች አሳልፎ የመስጠት ትልቅ ሃላፊነት አለበት” ብለዋል በአደራ ጭምር በማሳሰብ፡፡
ሰራዊቱ ከድል በኋላ ከሚመጣ መከፋፈል ራሱን እንዲጠብቅ እና አንጃ እንዳይፈጠርም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው ያሳሰቡት፡፡
“በጦርነት ያገኘነው አንድነት እና ወንድማማች ስሜት መቀጠል አለበት”ም ብለዋል፡፡
ድሉ በልማት መደገም እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
“እናንተ ጀግኖች የምለምናችሁ እንዳትፎክሩ ነው ጀግና አይፎክርም አይኩራራም ያደርጋል እንጂ አይኩራራም”ም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ጦሩ አንድ ሆኖ ሰራዊቱን በተሻለ እንዲገነባም በአጽኦት ተናግረዋል፡፡