“ኮ/ል መንግስቱ ከሀገር የወጡበት ጉዳይ ቢጠና የማጭበርበር ውጤት አካል እንደሚሆን ጥርጣሬ የለኝም”- ጠ/ሚ ዐቢይ
ጠ/ሚ/ር ዐቢይ “ሀገራችን አንድ ናት፤ ለመሸሽ ያዘጋጀነው ሀገር የለም” ብለዋል
ጠ/ሚ/ር ዐብይ አሁን እየተካሄደ ያለው ነገር በ1983 ዓ.ም ከተካሄደው ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ገልጸዋል
የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት እና የደርጉ መሪ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም እንዴት ከሀገር ወጡ የሚለው ጉዳይ ቢጠና የማጭበርበር ውጤት አካል እንደሚሆን ጥርጣሬ እንደሌላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በነበረው “የአዲስ ወግ መርሃ ግብር” ላይ በ1983 ዓ.ም ነበረውን የመንግስት ለውጥ አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አሁን በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው ሁኔታ በ 1983 ዓ.ም ኢትዮጵያ ላይ መካሄዱን ገልጸዋል፡፡
በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ አመራር እርስ በእርስ እንዲከፋፈል ተደርጎ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ “በዚያን ጊዜ አንዳንድ መሪዎች ከሀገር ሲወጡ ህወሃት ያለውጊያ አዲስ አበባ መግባቱን” አስታውሰው ገልጸዋል፡፡ በ 1983 ዓ.ም ከአዲስ አበባ 100፣ 150፣ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ውጊያ ሳይደረግ የመንግስት ለውጥ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
“እኛ ቢያንስ አዲስ ታሪካ ባንሰራ ከ1983 ታሪክ ልንማር እንደምንችል አልተገነዘቡም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ሁሉም ነገር እንዳበቃ የሚገልጹ አካላት መኖራቸውንና ከሀገር እንዲወጣ የሚመክሩ ኃይሎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
ከሰሞኑ አዲስ አበባ ስለተከበበ ነገሩ አልቋልና ከሀገር ሽሹ የሚሉ መከሪዎች መኖራቸውን ጠቅሰው በሌላ በኩል ግለሰቦች ከአዲስ አበባ ሊወጡ ነው የሚሉ ዘመቻዎችም እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “እኛ ሁለት ሀገር የለንም አየር ሲቀያየር የሚቀያየር ነገር የለንም” ያሉ ሲሆን አሁን ካልወጣን ያሉት ሃይሎች በጥቂት ሳምንታት እንግባ ብለው ጥያቄ እንደሚያቀርቡና ይህም በተግባር እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡
በ 1983 ዓ.ም የነበረውን የመንግስት ለውጥ ያከናወኑት (ዲዛይን የሰሩት) ሰዎች ድጋሚ ያንን አይነት ስራ ለመስራት (ዲዛይን ለመስራት) በማሸበር የሚነቃነቅ መንግስት እንዳለ ማሰብ እንደሌለባቸውም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
ስማቸውን ያልጠቀሷቸውን እነዚህን አካላት ”አዳዲስ ስትራቴጅ ይቀይሱ በዛኛው ስትራቴጅ አንሸወድም”ብለዋል፡፡
“አንዳንድ ኃይሎች” በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ መፈንቅለ መንግስት ስለሚካሄድ “ቶሎ ቶሎ እንውጣ” የሚል አስተያየት እየሰጡ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈነቀል መንግስት እንደሌለ ነገር ግን ይህንን መንግስት ሕዝቡ ካልፈለገው በማንኛውም ሰዓት ሊያነሳው እንደሚችል አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠው የኢትዮጵያ ሉዓላዊ መንግሥት በሚፈተን ግን በማይቀለበስ የለውጥ ጉዞ ላይ እንደሆነም በመርሃ ግብሩ ላይ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ጊዜያዊ ችግሮችን ለመፍታት እና የልማት ግቦችን ለማሳካት ከኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር ገንቢ በሆነ መልኩ ለመሥራት ምንጊዜም ዝግጁ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጦርነት የማጭበርበር ጦርነት እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ያለው ሁኔታ በ 1983 ዓ.ም ከነበረው ሁኔታ ጋር የተመሳሰለ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት እና የደርጉ መሪ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም እንደት ከሀገር ወጡ የሚለው ጉዳይ ቢጠና የማጭበርበር ውጤት አካል እንደሚሆን ጥርጣሬ እንደሌላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በደርግ ዘመነ መንግስት የማስታወቂያ ኮሚቴ አባል፤ የወታደራዊ ፖለቲካ ጠቅላይ ፕሮፖጋንዳ ኃላፊ የነበሩት እና “ነበር” የሚለውን ጨምሮ በርካታ መጽሐፍትን የደረሱት ገስጥ ተጫኔ ከሳምንታት በፊትከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅት በ1969 ዓ.ም ከገጠማት ጋር እንደሚመሳሰል መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በፌደራል መንግስት የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል አለመግባባት የተፈጠረው፤ ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲያስተዳድር የነበረውየገዥ ፓርቲ ግን ባሮች በመዋሃድ ብልጽግና ፓርቲን ሲመሰርቱ ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ብሎ በማፈንገጡ ነው።
ህወሓት የፌደራል መንግስቱ ህገወጥ ነው ያለውን ምርጫ ማካሄዱም የአልመግባባቱ ጡዘት ውጤት ነበር።
በሁለቱ አካላት መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ወታራዊ ግጭት ያመራው፤ ጥቅምት 24፣2013ዓ.ም ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነበር፡፡
ክህደት ፈጽሟል ባለው ህወሓት ላይ “የህግ ማስከበር ዘመቻ” በማወጅ የትግራይ ዋና ከተማና ብዙ ቦታዎችን መያዝ የቻለው መንግስት ከ8 ወራት በኋላ ለትግራይ ህዝብ የጽሞና ግዜ ለመስጠት በማሰብ ከትግራይ ክልል ሰራዊቱን ማስወጣቱ ይታወሳል። በክልሉ በነበረው ጦርነት ወቅት ዜጎች መፈናቃላቸውንና መገደላቸውን ኢሰመኮና ሌሎች አለምአቀፍ ተቋማት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
መንግስት ጦሩን ከክልሉ ማስወጣቱን ተከትሎ፣ ሕወሓት ወደ አማራ አፋር ክልል በመግባት ጥቃት በመሰንዘር፤ ሰዎች እንዲገደሉና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ማድረጉን መንግስት ገልጿል። አሁን ጦርነት ባለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ህዝብ ለርሃብና ለሞት አደጋ የተዳረገ ሲሆን በ100ሺዎች የሚቆጠር ሰውም ጦርነቱን በመሸሽ እየተፈናቀሉ መሆናቸውን መንግስት እየገለጸ ይገኛሉ፡፡
መንግስት በኢትዮጵያ በሽብር የተፈረጀው ህወሓት ደቅኖታል ያለውን ሉአላዊነትን ችግር ውስጥ የሚያስገባ አደጋ ለመቀልበስ ባለፈው ሳምንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።
በአፍካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሰጉን ኦባሳንጆ፣ በኢትዮጵያ አንድ አመት ያስቆጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡