ጠ/ሚ ዐቢይ በወሎ ግንባር በነበረው ውጊያ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ኃይሎች መሳተፋቸውን ገለጹ
ጦርነቱ ከአንድ ወገን ጋር ብቻ እንዳልሆነ በመረዳት ዋጋ ለመክፈል ያለውን ፍቅር በተግባር ሊገልጽ ይገባል ብለዋል
በቅስቀሳ የመጣውን የህዝብ ኃይል ለማስተናገድ በመንግስት በኩል በቂ ዝግጅት እንዳልነበርም ተናግረዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በጦርነቱ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ እና የኢትዮጵያ ዝርያ የሌላቸው ነጮች እና ጥቁሮች ከህወሓት ጋር መሳተፋቸውን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ህወሓት የከፈተውን ጦርነት እና ጦርነቱን እየመራበት ያለው ህዝባዊ አካሄድ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያም፣ ህዝብ ለመከላከያ ሠራዊቱ ያሳየው ድጋፍ የሚበረታታ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ሆኖም ግን በቅስቀሳ የመጣውን የህዝብ ኃይል ለማስተናገድ በመንግስት በኩል በቂ ዝግጅት እንዳልነበርም ተናግረዋል።
አሁን ላይ ከዛ ሁኔታ እርምት ተወስዶ ስትራቴጂካዊ በሆነ መልኩ እየተሰራበት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ ገልጸዋል
ኢትዮጵያ የገጠመችው ጦርነት ከአንድ ወገን ጋር ብቻ እንዳልሆነ በመረዳት ዋጋ ለመክፈል ያለውን ፍቅር በተግባር ሊገልጽ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ካለምንም ጥርጥር ኢትዮጵያ ጦርነቱን ታሸንፋለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አስታውቀዋል፡፡
ለማሸነፍ ቁልፉ እጃችን ላይ ነው ያለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷አንድ መሆን ቀን ከሌት መስራት፣ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆንን አካተው ገልጸዋል፡፡
የምናሸንፍበት እድል ግን የምናገኘነው ከጠላት መሆኑን ጠቅሰው ÷ መረጃ እና ፕሮፓጋንዳ በመጠቀም ማሸንፍ እንደሚቻል አንስተዋል፡፡
ጦርነት የፖለቲካ እሳቤ ማስጠበቂያ የመጨረሻ መንገድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ውጊያ በየትኛውም ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ገልፀው ጦርነቱን ግን ኢትዮጵያ እንደምታሸንፍ አትጠራጠሩ ብለዋል።