አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታነት ተነስተዋል
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ የደህንነት አማካሪ የነበሩት ገዱ አንዳርጋቸው ከኃላፊነት መነሳታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በኃላፊነት ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ በመጀመሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኋላም ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር፡፡
ከተሾሙበት ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን በብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች ላይ ሲያማክሩ ቆይተዋል፡፡
ሆኖም አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከብሔራዊ ደህንነት አማካሪነታቸው መነሳታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጽህፈት ቤት ዛሬ አርብ ግንቦት 27 ቀን 2014 ዓ/ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አምባሳደር ሬድዋን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ተክተው በብሔራዊ ደህንነት አማካሪነት መሾማቸውንም አስታውቋል፡፡
ከ2010ሩ ለውጥ ወዲህ በኤርትራ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት አምባሳደር ሬድዋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር፡፡
የቀድሞው የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ በአምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መተካታቸውን ያስታወቀው ጽህፈት ቤቱ የተሰጣቸው ሌላ ሹመት ወይም የተመደቡበት ሌላ ኃላፊነት እንዳለ የገለጸው ነገር የለም፡፡
የመሪው ብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ ገዱ ፓርቲው በቅርቡ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ሳይመረጡ መቅረታቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ኃላፊነት በተጨማሪ ሌሎች ኃላፊነቶችንም ሰጥተዋል፡፡
በዚህም አቶ ካሊድ አብዱራሂማን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የፕሮጄክቶች ክትትል፣ አቶ ወንድሙ ሴታ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ እንዲሁም አቶ ሄኖስ ወርቁን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አድርገው ሾመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በተጨሪም ወ/ሮ መሰረት ዳምጤን የፌደራል ዋና ኦዲተር፣ አቶ አበራ ታደሰ ደግሞ ምክትል ዋና ኦዲተር አድርገው በመሾም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያጸድቅላቸው ጠይቀዋል፡፡