የጸጥታው ምክር ቤት፤ በኢትዮጵያ ግጭቶች ቆመው ተኩስ ለማቆም የሚያስችል ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ
በአፍሪካ ህብረት የሚደረጉ የሰላም ጥረቶችን እደግፋለሁም ነው ምር ቤቱ ያለው
ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ነፃነት እና የግዛት አንድነት ቁርጠኛ አቋም እንዳለው አስታውቋል
ትናንት በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ አስቸኳይ ስብሰባን ያደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ግጭቶች ቆመው ተኩስ ለማቆም የሚያስችል ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ፡፡
ምክር ቤቱ ስብሰባውን በተመለከተ በፕሬዝዳንቱ ዡዋን ራሞን ዴላ ፉዬንቴ ራሚሬዝ (ሜክሲኮ) በኩል መግለጫ አውጥቷል፡፡
የሰሜኑ ግጭት መስፋፋት እጅግ አሳስቦናል ያሉ የምክር ቤቱ አባላት ግጭቱ በሰብዓዊ አቅርቦት እና በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ሊያሳድር በሚችለው ተጽዕኖ የምር ሰግተናል ማለታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
ለሁኔታው ምላሽ ለመስጠት በተመድ ዋና ጸሃፊ በኩል የተደረጉ ጥረቶችን መቀበላቸውን የገለጹት አባላቱ ሁኔታውን የበለጠ ከሚያጋግሉ የጥላቻ እና ከፋፋይ ንግግሮች ብንቆጠብ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መንግስት ኤምባሲዎች አዲስ አበባ እንደ ተከበበች በማስመሰል ከሚነዙት ሀሰተኛ መረጃ ኢንዲቆጠቡ አሳሰበ
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግጋት እንዲከበሩ፣ የህዝብ መገልገያዎች ስራ እንዲጀምሩ እና ያልተቆራረጠ የሰብዓዊ አቅርቦት እንዲኖርም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ግጭቶች ቆመው ተኩስ ለማቆም የሚያስችል ስምምነት እንዲደረግ፤ ቀውሱን ለመፍታትና በመላ ሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሚበጅ አሳታፊ ብሄራዊ ውይይት ለመጀመር የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዲመቻቹም ጠይቀዋል።
ይህን ጨምሮ ሌሎች ቀጣናዊ ግጭቶችን በመፍታት ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት አፍሪካ ህብረትን በመሰሉ ተቋም የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚደግፉም አባላቱ ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ተወካይ ሆነው ለተመረጡት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ስራዎች ድጋፍ አለንም ነው አባላቱ ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከ10 ለበለጡ ጊዜያት የተሰበሰበው ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ነፃነት እና የግዛት አንድነት ቁርጠኛ አቋም እንዳለው አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ ከአሁን ቀደም በአየር ላንድ ጥሪ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መምከሩ የሚታወስ ነው፡፡