“በአዲስ አበባ እና በሰሜን ያሉ ሁሉም መሪዎች ችግራቸው ፖለቲካዊ እንደሆነና ፖለቲካዊ መፍትሄን እንደሚፈልግ በግለሰብ ደረጃ ተስማምተዋል”- ኦባሳንጆ
ኦባሳንጆ ትናንት በኢትዮጵያ በማድረግ ላይ ያሉትን የሰላም ጥረት በተመለከተ ለጸጥታው ምክር ቤት ማብራሪያ ሰጥተዋል
ኦባሳንጆ ዛሬ ከአማራ እና ከአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ጋር ተገናኝተው ይመክራሉ
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴገን ኦባሳንጆ ዛሬ ጥቅምት 30 ቀን 2014 ዓ/ም ከአማራ እና ከአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደሮች ጋር እንደሚገናኙ ተናገሩ፡፡
ኦባሳንጆ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት ረግቦ ወደ ሰላም መምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመመከር ከዶ/ር ይልቃል ከፋለ እና ከአቶ አወል አርባ ጋር የሚገናኙት፡፡
ይህንንም የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ትናንት በወቅታዊ የአፍሪካ የጸጥታ ሁኔታዎች ላይ ለመከረው የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ በመደረግ ላይ ስላሉ የሰላም ጥረቶች ገለጻ አድርገዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የጸጥታው ምክር ቤት፤ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ኦባሳንጆ ገለጻ ተደረገለት
በገለጻቸው በሱዳን የነበራቸውን ጉብኝት አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ከፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር መነጋገራቸውን አስታውቀዋል፡፡
ውጥረቱን ለማርገብ እና ለቀጣይ ውይይቶች ምቹ መደላድልን ለመፍጠር የሚያስችል ፍሬያማ ንግግር ማድረጋቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ከተነጋገሩና ወደ ትግራይ እንዲያቀኑ ከተስማሙ በኋላ እሁድ ጥቅምት 28 ቀን 2014 ዓ/ም በመቀሌ ደብረጽዮን ገብረሚካዔልን (ዶ/ር) ጨምሮ በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውጥረቱን ለማርገብና አመርቂ መፍትሄዎችን ለመፈለግ የሚያስችል ምክክር ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ እና በሰሜን ያሉ ሁሉም መሪዎች በመካከላቸው ያለው ችግር ፖለቲካዊ እንደሆነና በውይይት ሊፈታ የሚችል ፖለቲካዊ መፍትሄን እንደሚፈልግ በግለሰብ ደረጃ መስማማታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ችግሩ የከፋ ማህበረ ምጣኔ ሃብታዊ እና ሰብዓዊ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን በመጠቆም ዘላቂ እልባት ለመስጠት መፍጠን ያስፈልጋልም ነው ኦባሳንጆ ያሉት፡፡
በመሆኑም የጸጥታው ምክር ቤት ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁመው ወደ ውይይት እንዲመጡ፣ ያልተቆራረጠ የሰብዓዊ እርዳታዎች አቅርቦት እንዲኖር፣ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ እና ሁሉን አካታች ብሔራዊ ውይይት በአፋጣኝ እንዲደረግ ግፊት እንዲያደርግና ሁኔታዎችን በአንክሮ እንዲከታተል አሳስበዋል፡፡
በስብሰባው ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በህወሓት የተፈጸመው የክህደት ስራ በእጅጉ የሚያሳዝንና ኢትዮጵያ በዚህ ወንጀለኛ ቡድን ያሳለፈችውን ጊዜ ለመርሳት የአንድ ትውልድ ጊዜ የሚፈጅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ትዊተር በኢትዮጵያ ላይ ገደቦችን መጣሉን አስታወቀ
አምባሳደሩ ቡድኑ ያን ሁሉ ደም መፋሰስ እንዲፈጠር ባያደርግ ኖሮ ፖለቲካዊ እጣ ፋንታውም ሆነ ሁኔታው በውይይት መፍትሄ ያገኝ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
“በአፍሪካዊ እገዛዎች ካለንበት ችግር መውጣት ጥሩ መፍትሄ ነው ብለን እናምናለን፤ ወደ ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚወስደው መንገድ ግን አልጋ በአልጋ ነው ወይም ቀላል ነው ማለት አይቻልም” ብለዋል አምባሳደሩ፡፡
መንግስት አሁን ላይ የህወሓትን መስፋፋት ማስቆምና በቡድኑ ጥቃት እየደረሰበት ያለውን ህዝብ መታደግ ላይ ትኩረት ማድረጉንም ለምክር ቤቱ ተናግረዋል፡፡