“ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሡ ሁሉ ለጊዜው የሚሳካላቸው ይምሰላቸው እንጂ መጨረሻቸው ኪሣራ ነው” - ጠ/ሚ ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትን አስተላልፈዋል
ሞተው እንደሚቀሩ ሃገራት አይደለችም ያሏት ኢትዮጵያ ጠላቶቿን እንደምታከስርና እንደምታሳፍርም ገልጸዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሡ ሁሉ ለጊዜው የሚሳካላቸው ይምሰላቸው እንጂ መጨረሻቸው ኪሣራ ነው” አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን ያሉት የትንሳዔ (ፋሲካ) በዓልን አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ነው፡፡
በመልዕክቱ የትንሳዔን እሳቤ በሰፊው የዳሰሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክህደት፣ ሤራና ፍርደ ገምድልነት ለጊዜው ያሸነፉ ቢመስሉም በመጨረሻ እንደሚሸነፉ በትዕምርታዊነት አስቀምጠዋል።
ክርስቶስ የዲያብሎስን ዓላማ ሳያውቁ በተላኩ ፈጻሚዎች ለመሰቀል መብቃቱን ያነሱም ሲሆን የላኪውም ሆነ የተላላኪዎቹ ተንኮል የተሳካው ክርስቶስ ከሙታን ተለይስቶ እስከተነሳበት እስከ ሶስተኛው ቀን ድረስ ብቻ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
ይህ በኢትዮጵያ ሊታይ የሚችልበት አንጻር እንዳለ መመልከቱ መልካም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ዛሬም ከኋላ ሆኖ ሀገራችንን ለማፍረስ ወጥመድ የሚያጠምድ፣ ተንኮል የሚሠራው ጠላት ማነው?” የሚል ጥያቄ አዘል መልዕክትን አስቀምጠዋል፡፡
“ሀገር ካላጠፋ በቀር አይረካም” ያሉት ይህ “ጥንተ ጠላት” የሚያሠማራቸው የጥፋት ተላላኪዎቹስ እነማን ናቸው? ሲሉም ለገንዘብ፣ ለጥቅም እና ለሥልጣን ብለው የሚላላኩት እነ ማን እንደሆኑም ይጠይቃሉ፤ እነሱንም ጭምር የሚያጠፋው ተልዕኳቸው የኢትዮጵያን ጥንተ ጠላት ፍላጎት ብቻ የሚያሳካ መሆኑን በመጠቆም፡፡
ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሡ ሁሉ ለጊዜው የሚሳካላቸው ይምሰላቸው እንጂ መጨረሻቸው ኪሣራ ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሞተው እንደሚቀሩ ሀገራት እንዳይደለች ይልቁንም ከሙታን ተነስታ ጠላቶቿን እንደምታሳፍር እና እንደምታከሥርም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው ያስቀመጡት፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ዛሬ ቅዳሜ ሚያዚያ 15 ቀን 2014 ዓ/ም ወደ ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን አቅንተው የማዕከላዊ ዕዝ ወታደራዊ አባላትን አግኝተዋል፡፡ በሰቆጣ ከተማ ከተለያዩ አካባቢዎች ከተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ትናንት ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ”በባይተዋሮችና ውል አልባ ኢትዮጵያውያን“ ይበልጥ እየተፈተነች መሆኑን በመጠቆም እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለውን ውሳኔ ማሳለፉን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡