ግለሰቡ ገፅታውን ቀይሮና ሴት መስሎ በመቅረብ ተበዳይን ውጭ ሀገር ስራ እንደሚያስቀጥራት በማሳመን ማጭበርበሩ ተገልጿል
ጾታውን ቀይሮ በመቅረብ 103ሺ ብር ያጭበረበረው ግለሰብ ተያዘ
ገፅታውን ቀይሮና ሴት መስሎ በመቅረብ ከአንዲት ግለሰብ ላይ 103 ሺ ብር አታሎ የወሰደው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ፡፡
ቺና በሚል ስም በሴት ፆታ የሚጠራው ግለሰብ በመዋቢያ ቁሶች (ሜካፕ) እና በሌሎች ነገሮች ራሱን የሴት ገፅታ አላብሶ ሲንቀሳቀስ እንደነበረ የገለጸው ፖሊስ በጋራ እንስራ በሚል የማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥሮት ነው በቁጥጥር ስር ያዋለው፡፡
ግለሰቡ ኳታር እና እንግሊዝ እንደኖረ ፣ አረብኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ እንደሚናገርም በምርመራ ማረጋገጡን ፖሊስ ይፋ አድርጓልለ፡፡ የግል ተበዳይ የሆነችው እየሩሳሌም ሰሎሞን በጓደኛዋ አማካይነት ቺናን እንደተዋወቀችው እና ወደ ውጪ ሀገር ወስዶ ስራ እንደሚያስቀጥራት የነገራት መሆኑን ያስታወቀው ፖሊስ እስከዚያው በጋራ ሱፐር ማርኬት ከፍተው እየሰሩ እንዲቆዩ ጠይቋት እንደነበርም ተረጋግጧል ብሏል፡፡
በተፈጠረው ቅርርብም ቺና ከአከራዩ ጋር እንዳልተስማማ እና ሌላ ማረፊያ ቤት እንደሚፈልግ ሲያማክራት እየሩሳሌምም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በተለምዶ ዘበኛ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ ዩፍቲኒ ፔንሲዮን ይዛው መጥታ እዚያ እንዲያርፍ እንዳደረገች ተገልጿል ፡፡
በጋራ ሱፐር ማርኬት ለመክፈት የተነሳውን ሃሳብ በተመለከተም ቺና እየሩሳሌምን ብር እንድታመጣ ሲጠይቃት ከተለያዩ ሰዎች በብድር ያገኘችውን 103 ሺ ብር እንደሰጠችውና እሱም የቀረውን እኔ እጨምርበታለሁ ማለቱን ይሁንና ከዚያ በኋላ ከፔንሲዮኑም ለቆ ወጥቶ ስልኩን መዝጋቱን ፖሊስ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
የግል ተበዳይ ለፖሊስ ካመለከተች በኋላ ተጠርጣሪው አዲስ አበባ ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ መያዙንና የሴት ገፅታ ተላብሶ የነበረው ቺና በፖሊስ በተደረገው ማጣራት ወንድ ሆኖ መገኘቱን ፖሊስ ገልጿል፡፡ የግል ተበዳይ እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ቺና ሴት እንጂ ወንድ መሆኑን በፍፁም አለማወቋ የተጠቀሰ ሲሆን የተፈፀመውን የማታለል ወንጀል በተመለከተ ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡