አቶ ልደቱ ለተመሰረተባቸው "ህገወጥ የጦር መሳርያ መያዝ" ክስ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ፍ/ቤት ቀርበዋል
ፖሊስ አቶ ልደቱን ለምን እንዳልፈታቸው እንዲያስረዳ ፍርድ ቤት አዘዘ
በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረዋል በሚል በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው ዛሬ በምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ቀርበዋል፡፡
አቶ ልደቱ ፍ/ቤት የቀረቡት በኦሮሚያ ክልል አቃቤ ህግ የተመሰረተባቸውን "ህገወጥ የጦር መሳርያ መያዝ" ከስ ምስክሮች ለመስማት እንደነበር የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለአል ዐይን ገልጸዋል።
ይሁንና አቃቤ ህግ ምስክሮችን ማቅረብ ያልቻለ ሲሆን ፍ/ቤቱ የቢሾፍቱ ወረዳ ፖሊስ ምስክሮቹን አስገድዶ እንዲያቀርብለት ትዕዛዝ ይጻፍልኝ በማለት ጠይቋል፡፡ በዚህም ግርድ ቤቱ ለጥቅምት 5/2013 ቀጠሮ ሰጥቷል።
አቶ አዳነ ለአል ዐይን እንደተናገሩት በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 02 ቀን 2013 ዓ.ም. አቶ ልደቱ እንዲፈቱ በፍርድ ቤት የተጻፈውን ትዕዛዝ ፖሊስ አልቀበልም ብሏል፡፡
አቶ ልደቱ በዋስ እንዲፈቱ የተሰጠውን ትዕዛዝ ፖሊስ አለማክበሩን እንዲሁም ለከፍተኛ ፍ/ቤት የቀረበው የይግባኝ ጥያቄም ውድቅ መደረጉን በተመለከተ ጠበቆቻቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
ፍ/ቤቱ ለቢሾፍቱ ፖሊስ የተጻፈው ትዕዛት በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በኩል እንዲደርስ ያዘዘ ሲሆን ፖሊስ በጥቅምት አምስቱ ቀጠሮ ቀርቦ ለምን እንዳልፈታቸው እንዲያስረዳም አዟል።