ፖላንድ ሩሲያ ላይ ማዕቀቦች እንዲጣሉ ግፊት ስታደርግ ነበር
ሩሲያ እና ዩክሬን እያደረጉት ያለውን ጦርነት ተከትሎ በሩሲያ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች ውጤታማ አለመሆናቸውን የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴስዝ ሞራዊኪ አሁን ላይ የሩሲያ መገበያያ ገንዘብ ሩብል መሻሻል ማሳየቱ የተጣሉት ዕቀቦች ውጤታማ አለመሆናቸውን እንደሚያመለክት ተናግረዋል፡፡ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት በሩሲያ ላይ በርካታ ማዕቀቦችን ቢጥሉም ማዕቀቦቹ ግን “ውጤታማ አይደሉም” ሲሉም ነው የፖላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር የገለጹት፡፡
“አሁን ላይ በግልጽ መናገር ያለብኝ ነገር የጣልናቸው ማዕቀቦች እስካሁን ምንም ጥቅም አልሰጡም” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ መሪዎች በሩሲያ ላይ የጣሏቸው ማዕቀቦች የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስ፣ የበጀትና የገንዘብ አቅምን እንደሚዳክም በመግለጽ ቢጥሉም ውጤት ግን እንደሌለውና ሩሲያ በተጠቀሱት ዘርፎች ምንም አልተጎዳችም ነው የተባለው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶ አቅራቢያ በዩክሬን ስደተኞች ማዕከል ባደረጉት ንግግር የተጣሉት ማዕቀቦች ምንም እንዳልፈየዱ ጮክ ብለን መናገር አለብን ብለዋል፡፡ የሩሲያ የመገበያያ ገንዘብ ሩብል ምንዛሬ መሻሻል ማዕቀቦቹ ውጤታማ አለመሆናቸውን ማረጋገጫ ነው ሲሉም ነው የፖላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያስታወቁት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው በሩሲያ ላይ ማዕቀቦችን መጣል ያስፈለገው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን እንዲያቆሙ ታልሞ ቢሆንም ይህ ግን አልሆነም ብለዋል፡፡
የሩሲያ እና የዩክሬንን ጦርነት ተከትሎ በሩሲያ ላይ ማዕቀቦች እንዲጣሉ ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ የቆየችው ፖላንድ ነበረች፡፡ ሞስኮ በምዕራባውያን ላይ በተጣሉባት ማዕቀቦች እንዳልተጎዳች ፖላንድ ገልጻለች፡፡