የፖላንድ ፕሬዝዳንት የተተኮሰው ሚሳይል ከዩክሬን አየር መከላከያ ሊሆን እንደሚችል ተናገሩ
በፖላንድ መንደር ውስጥ ሁለት ሚሳይሎች መተኮሳቸውን ተከትሎ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ውጥረት እንደተፈጠረ ይታወቃል
በፖላንድ መንደር ውስጥ ለወደቁት ሚሳይሎች በርካቶች ጣታቸውን ሩሲያ ላይ ቀስረው እንደነበር አይዘነጋም
ትናንት ማክሰኞ ምሽት ለዩክሬን ድንበር ቅርብ በሆነች የፖላንድ መንደር ውስጥ ሁለት ሚሳይሎች መተኮሳቸውን ተከትሎ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ውጥረት እንደተፈጠረ የሚታወቅ ነው፡፡
በዚህም አላበቃም በርካቶች የሁለት ሲቪሎችን ህይወትን ለቀጠፉት የሚሳይሎች ተኩስ ጣታቸውን ሩሲያ ላይ ሲቀስሩ ተስተውሏል፡፡ ይሁን እንጅ ሞስኮ ፖላንድ መንደር ውስጥ ለወደቁት ሚሳይሎች ኃላፊነት አልወስድም ስትል ተደምጣለች፡፡
“ሩሲያ በዩክሬን እና በፖላንድ ድንበር ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት አልከፈተችም''ም ነበር ያለቸው ሩሲያ በመከላከያ ሚኒስትሯ በኩል በሰጠችው ምላሽ፡፡
በሩሲያ ላይ የቀረበው ክስ ''ሆነ ተብሎ ሁኔታውን ለማባባስ የተደረገ ነው'' ሲሉም ነበር የተናገሩት ሚኒስትሩ ጄኔራል ሰርጌይ ሾይጉ፡፡
በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ሲያካሂዱ የቆዩት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው የተተኮሱት ሚሳዔሎች ከሩሲያ የመሆናቸው እድል ዝቅተኛ ነው ብለው ነበር፡፡
''ምርመራችንን ሙሉ በሙሉ እስከምናጠናቅቅ ብዙ መናገር አልፈልግም፤ ነገር ግን መስመሩን ተመልክተን ከሩሲያ የተተኮሰ የመሆነ ዕድሉ ጠባብ መሆኑን መናገር ይቻላል'' ሲሉም ነበር የተናገሩት ጆ-ባይደን፡፡
ጆ-ባይደን ያሉት አልቀረም አሁን ላይ የፖላንዱ ፕሬዝዳንት አንድሬ ዱዳ የእሳቸውን (ባይደን) ግምት የሚያጠናክር መረጃ ይፋ አድርገዋል፡፡
ሚሳዔሎቹ የተተኮሱት ከዩክሬን አየር መከላከያ የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ነው ማለታቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
"ይህ በፖላንድ ላይ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑን በፍጹም ምንም የሚያመላክት ነገር የለም... በጸረ ሚሳኤል መከላከያ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለው ሮኬት ሳይሆን አይቀርም፣ ይህም ማለት በዩክሬን መከላከያ ሃይል ተጠቅሞበታል" ሲሉም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።