ባለቤቷ ወደ ግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና የተላከባት ዩክሬናዊት እራሷን በእሳት አቃጠለች
ግለሰቧ በራሷ ላይ አሰቃቂውን ድርጊት የፈጸመችው በኬቭ ክልል በሚገኝ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ነው
ዩክሬን ባጋጠማት የወታደር እጥረት በየወሩ 30 ሺ ዜጎችን እየመለመለች ትገኛለች
ባለቤቷ በዩክሬን የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ የተወሰደባት ዩክሬናዊት እራሷን በእሳት አቃጠለች፡፡
ባሳለፍነው ሀሙስ በኬቭ ክልል ወደ ሚገኝው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀናችው እንስት ከቦርሳዋ ውስጥ ያወጣችውን ተቀጣጣይ ኬሚካል በሰውነቷ ላይ በማፍሰስ እራሷን በእሳት አንድዳለች፡፡
በአካባቢው የነበሩ ሶስት የፍርድ ቤቱ የጥበቃ ሰራተኞች በግለሰቧ ሰውነት ላይ የተያያዘውን ወላፈን በእሳት ማጥፊያ ለማጥፋት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡
ሆኖም እሳቱ ሙሉ ለሙሉ ከመጥፋቱ በፊት 70 በመቶ የሰውነት ክፍሏ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ከአደጋው በኋላ የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡
ድርጊቱን ተከትሎ ግለሰቧ በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል የተወሰደች ሲሆን በአሁኑ ወቅት በጽኑ ህሙማን ማቆያ ውስጥ ህይወቷን ለማትረፍ ሀኪሞች እርብርብ እያደረጉ እንደሚገኙ ነው የተሰማው፡፡
ፖሊስ ከአደጋው በኋላ አገኝሁት ባለው መረጃ ግለሰቧ እና በውትድርና ላይ የሚገኝው ባለቤቷ በፍቺ ሂደት ላይ ያሉ መሆናቸውን እንዲሁም ልጃቸውን በየትኛው ወላጅ ስር ሆኖ ይደግ በሚለው ጉዳይ ላይ በፍርድ ቤት ክርክር ላይ እንደነበሩ አስታውቋል፡፡
ከፍተኛ ወታደራዊ እጥረት እንዳጋጠማት በሚነገርላት ዩክሬን እድሜው እና አካለዊ ሁኔታው ለውትድርና ብቁ የሆነ ዩክሬናው ሁሉ በግዳጅ መከላከያውን እንዲቀላለቀል ምልመላ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ዜጎች የግዳጅ ምልመላውን ለማምለጥ አካል ጉዳተኛ እንደሆኑ ከማስመል ጀምሮ እራሳቸውን በእድሜ እንደገፋ ሰው በማስመሰል ከሀገር ለመውጣት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደርጋሉ፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልደሚር ዘለንስኪ በተከታታይነት በፈረሟቸው ህጎች የምልመላ እድሜ ከ27 ወደ 25 ዝቅ እንዲል ያደረጉ ሲሆን፤ ይህን የምልመላ ሂደት በተለያዩ ምክንያቶች ለማምለጥ እና ለማጭበርበር በሚጥሩ ዩክሬናውያን ላይ ጠበቅ ያለ ቅጣት እንዲተላለፍ ወስነዋል፡፡
ለሁለት አመታት በዘለቀው ጦርነት በሩሲያ ብልጫ የተወሰደባቸው ፕሬዝዳንቱ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ዜጎች በተጨማሪ በውጭ የሚገኙ ዩክሬናውያንም ወደ ሀገራቸው ተመልሳችሁ ሉአላዊነታችሁን አስከብሩ ሲሉ በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር በቅርቡ ባወጣው በገለልተኛ አካል ባልተረጋገጠ መረጃ 50 ሺህ የዩክሬን ወታደሮች በየወሩ እንደሚሞቱ እና ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስናግዱ አስታውቋል፡፡
በአንጻሩ ዩክሬን ያጋጠማትን የወታደር እጥረት ለመሙላት በምታደርገው የግዳጅ እና በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ምልመላ በየወሩ 30ሺህ ዜጎችን ወደ መከላከያው እንዲቀላቀሉ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡