ዩክሬን ድርድር ለማድረግ ወኔ ሊኖራት ይገባል ሲሉ ፖፕ ፍራንሲስ ተናገሩ
የ87 አመቱ ጳጳስ ባለፈው አመት በጣሊያናዊው ካርዲናል ማቲዩ ዘፒ የተመራ የሰላም ልኡክ ወደ ኪቭ፣ ሞስኮ እና አሜሪካ ልከው ነበር
የሮማው ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ዩክሬን ግጭቱን ለማቆም "ነጭ ሰንደቅ አላማ" ከፍ የማድረግ እና ከሩሲያ ጋር የመደራደር ወኔ ሊኖራት ይገባል ብለዋል
የሮማው ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ዩክሬን ግጭቱን ለማቆም "ነጭ ሰንደቅ አላማ" ከፍ የማድረግ እና ከሩሲያ ጋር የመደራደር ወኔ ሊኖራት ይገባል ብለዋል።
ፖፕ ፍራንሲስ ይህን ያሉት ባለፈው ወር ከስዊስ ብሮድካስተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
የዩክሬኑን ፕሬዝደንት ዘለንስኪን ባለፈው አርብ እለት በኢስታንቡል ያስተናገደችው ቱርኩም አዲስ የላደራድራችሁ ሀሳብ ማቅረቧን ዘገባው ጠቅሷል። ዘለንስኪ ሰላም እንደሚፈልጉ ነገርግን ምንም አይነት ግዛት አሳልፈው እንደማይሰጡ በተጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣሉ።
የዩክሬን መሪዎች የሰላም እቅድ የሩሲያ ጦር ሙሉ በሙሉ ከዩክሬን ግዛት እንዲወጣ እና የዩክሬን ድንበር ከጦርነት በፊት ወደነበረበት እንዲመልስ ጥሪ የሚያቀርብ ነው።
ነገርግን ክሬሚሊን ዩክሬን ባስቀመጠችው ቅድመ ሁኔታ እንደማትስማማ ገልጻለች።
ፖፕ ፍራሲስ በዚሁ ቃለ ምልልስ "መደራደር ወኔ የሚያስፈልገው ነው። መሸነፍክን ስታስብ ነገሮች በጥሩ ሁኔታ አይሄዱም፤ የመደራደመር ወኔ ሊኖርህ ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል።
ፖፕ ፍራንሲስ ከዚህ በፊት ስለዩክሬን ጦርነት በሰጡት ቃለ ምልልስ ስለድርድር ቢያወሱም "ነጭ ሰንደቅ አላማ" እና "ሽንፈት" የሚሉትን ቃላት ሲጠቀሙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው ተብሏል።
የ87 አመቱ ጳጳስ ባለፈው አመት በጣሊያናዊው ካርዲናል ማቲዩ ዘፒ የተመራ የሰላም ልኡክ ወደ ኪቭ፣ ሞስኮ እና አሜሪካ ልከው ነበር።
"ጦርነቱ የሚያበቃው ስንት ሰው ሲሞት ነው?፤ አደራዳሪ ሀገር ፈልጋችሁ በጊዜ ተደራደሩ" ያሉት ጳጳሱ ለማደራደር ፍላጎት ያላትን ቱርክ ጠቅሰዋል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ሁለት አመት ያለፈው ሲሆን ሩሲያ በቅርብ ወራት ውስጥ በምስራቅ ዩክሬን አቭዲቪካ የተባለችውን ወሳኝ ከተማ ጨምሮ በርካታ መንደሮችን መቆጣጠር ችላለች።
ዩክሬን እነዚህን ቦታዎች ለመልቀቅ የተገደደችው የምዕራባውያን የጦር መሳሪያ ድጋፍ በቶሎ ባለመድረሱ ነው የሚል ምክንያት ማቅረቧ ይታወሳል።